ታሊባን የውጭ ሃገር ገንዘብ አፍጋኒስታን ውስጥ ጥቅም ላይ እንዳይውል አዘዘ

የውጭ ምንዛሬ የሚቀይሩ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታሊባን አፍጋኒስታን ውስጥ የውጭ ሃገራት መገበያያ ገንዘቦች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ከልክሏል፤ ይህም ቋፍ ላይ ያለውን የሃሪቱን ምጣኔ ሃብት ይጎዳዋል የሚል ስጋት ጭሯል።

"የምጣኔ ሃብታችን ሁኔታና ብሔራዊ ጥቅማችን እያንዳንዱ አፍጋናዊ የአፍጋን ገንዘብ ለመገበያያነት እንዲጠቀም ያስገድዳል" ብሏል ታሊባን።

ታሊባን ተመልሶ ከአሜሪካ እጅ አ ፍጋኒስታንን ማስተዳደር ከጀመረ በኋላ ዓለም አቀፍ የገንዘብ እርዳታዎች በመቆማቸው የአፍጋኒስታን ምጣኔ ሃብት እየተንገዳገደ ይገኛል።

የዩናይትድ ስቴትስ ዶላር በአፍጋኒስታን ገበያዎች ጥቅም ላይ ሲውል ማየት የተለመደ ነው።

አልፎም አፍጋኒስታንና ፓኪስታን የሚዋሰኑበት ድንበር ላይ ንግድ የሚጦፈው በዶላር እገዛ ነው።

"ኢስላማዊ ኤሜሬት ሁሉም ዜጎች፣ ባለሱቆች፣ ነጋዴዎች፣ እንዲሁም ሸማቹ ማሕበረሰብ ከዚህ በኋላ በአፋጋኒ [የአፍጋኒስታን ገንዘብ] እንዲጠቀምና የውጭ ሃገራት ገንዘቦችን ከመጠቀም እንዲቆጠብ እናሳስባለን" ሲሉ የታሊባን ቃል አቀባይ ዛበቢሁላህ ሙጃሂድ መግለጫ ለቀዋል።

"ይህንን መመሪያ ጥሶ የተገኘ ቅጣት ይጠብቀዋል" የሚል ቀጭን ትዕዛዝ መግለጫው ተካቷል።

ባለፈው ሰኔ ታሊባን አፍጋኒስታንን ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ በውጭ ሃገራት የሚገኙ ቢሊዮን ዶላሮች የሚያወጡ የአፍጋኒስታን ንብረቶች በአሜሪካና በአውሮፓ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎባቸዋል።

"ታሊባን ላይ ቅጣት ማስተላለፋችን አስፈላጊ ነገር ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ በሃገሪቱ ላለው ሰብዓዊ ቀውስ መፍትሄ መፈለግ አለብን። ይህንን ነው እያደረግን ያለነው።

የአፍጋኒስታንን ሕዝብ ለመርዳት" ሲሉ የአሜሪካ ግምዣ ቤት ምክትል ኃላፊ ዋሊ አዴየሞ ባለፈው ወር ተናግረው ነበር።

ታሊባን፤ አፍጋኒስታን ከበድ ያለ የጥሬ ገንዘብ እጥረት ላይ ባለችበት ወቅት የአፍጋኒስታንን ንብረቶች ማገድ ተገቢ አይደለም ሲል እንዲለቀቅለት ጠይቆ ነበር።

ከዚህ በፊት የአፍጋኒስታን ወጪ ሶስት አራተኛ የሚሸፍኑ የነበሩት የውጭ ሃገራት እርዳታዎች አሁን የሉም።

በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት መባቻ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም [አይኤምኤፍ] አፍጋኒስታን የኔን ንብረቶች መጠቀም አትችልም ማለቱ ይታወሳል። የዓለም ባንክም ቢሆንም ለሃገሪቱ ፕሮጀክቶች የሚሰጠውን ብድር ነስቷል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የሃገሪቱ ምጣኔ ሃብት 30 በመቶ ዘቅጦ ሚሊዮኖች ወደ ድህነት አረንቋ እንደሚገቡ አስጠንቅቋል።

በዚህ የምጣኔ ሃብት ቀውስ ምክንያት የጎረቤት ሃገራትም ጭምር ከአፍጋኒስታን በሚመጡ ስደተኞች ምክንያት ችግር ላይ ይወድቃሉ ሲል ተቋሙ ተንብይዋል።

አፍጋኒስታን ይህ አልበቃ ብሏት ድርቅ ተከስቶባት በርካታ ሰብል ሳይታጨድ ወድሟል።

ምንም እንኳ የአውሮፓ ሃገራት በሃገሪቱ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ እናስወግዳለን ቢሉም ለታሊባን እውቅና ከመስጠት የበለጠባቸው አይመስልም።