የምሥራቅ አፍሪካ መሪዎች በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዲቆም ጠየቁ

የኬንያው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የኡጋንዳ አቻቸው ዩዌሪ ሙሴቪኒ

የፎቶው ባለመብት, STR

የምስሉ መግለጫ,

የኬንያው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የኡጋንዳ አቻቸው ዩዌሪ ሙሴቪኒ

የምሥራቅ አፍሪካ አገራት መሪዎች በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዲቆም እና የጦርነቱ ተሳታፊዎች ግጭቱን በውይይት እንዲፈቱ ጠየቁ።

የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ በኢትዮጵያ ጉዳይ ለመምከር የምሥራቅ አፍሪካ ማኅብረሰብ አገራትን ስበሰባ ጠርተዋል።

ሙሴቪኒ የፊታችን ኅዳር 07/2014 ዓ.ም እንዲካሄድ በጠሩት ሰበሰባ የኬንያ፣ የሩዋንዳ፣ የደቡብ ሱዳን እና ታንዛኒያ ተወካዮች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በበኩላቸው ትናንት ባወጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው "ግጭት መቆም አለበት" ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ፕሬዝዳንት ኬንያታ፤ የግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ተኩስ አቁምው ዘላቂ ለሆነ ሰላም መነጋገር አለባቸውም ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ተቋም (ኢጋድ) በአስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቋል።

ኢጋድ ሁሉም አካላት ከግጭት እንዲቆጠቡ እና ልዩነቶችን በውይይት እንዲፈቱ ጠይቋል።

በተመሳሳይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ትናንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በስልክ መነጋገራቸውንና ለድርድር የሚሆን ማንኛውንም ድጋፍ እንደሚሰጡ እንደገለጹላቸው በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል።

የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን እየተባባሰ ለመጣው ጦርነት መላ ለመሻት ዛሬ አዲስ አበባ መግባታቸው ታውቋል።

ፌልትማን አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ጋር ተወያይተዋል።

ሙሳ ፋኪ ከአምባሳደሩ ጋር በወቅታዊ የኢትዮጵያ እና የሱዳን ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል።

የህወሓት አማጺያን የደቡብ ወሎ ከተሞች የሆኑትን ደሴንና ኮምቦልቻን ተቆጣጥረው ተከትሎ በሰሜን ኢትዮጵያ ለአንድ ዓመት ሲካሄድ የቆየው አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ እየተነገረ ነው።

መንግሥት የአማጺያኑ እንቅስቃሴ ለመግታት አቅም ያለው በሙሉ ወደ ጦርነቱ አካባቢ እንዲዘምት ጥሪ በማድረግ ሠራዊቱን እያንቀሳቀሰ ሲሆን አማጺያኑም ግፊታቸውን መቀጠላቸውን እየተናገሩ ነው።

በመዲናዋ በአዲስ አበባ ያለው የደኅንነት ቁጥጥር የተጠናከረ ሲሆን የጦር መሳሪያ ያላቸው ነዋሪዎች ለመንግሥት እንዲያስመዘግቡ ተጠይቀዋል።

ባለፈው ማከስኞ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገገ ሲሆን የአገሪቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም አዋጁን ዛሬ አጽድቆታል።