ሰላም እንዲወርድ ህወሓት ከያዛቸው ቦታዎች መውጣት እንዳለበት መንግሥት ገለጸ

የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
የምስሉ መግለጫ,

የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

አንድ ዓመት ያስቆጠረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ቆሞ ሰላም እንዲወርድ ከተፈለገ ህወሓት ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች መውጣት አለበት ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ ሰላም እንዲወርድ ህወሓት ሦስት ነገሮችን መፈጸም አለበት ብለዋል።

እንደ አምባሳደሩ መግለጫ "ሰላም እንዲወርድ" ህወሓት ከያዛቸው የአማራ እና የአፋር አካባቢዎች መውጣት አለበት። በሁለተኛ ደረጃ ህወሓት ለፌደራሉ መንግሥት ሕጋዊነት እውቅና መስጠት እና መቀበለ አለበት ብለዋል። ሦስተኛው ነጥብ ደግሞ ህወሓት ኃይሎቹ የሚፈጽሟቸውን ጥቃቶች ማቆም አለባቸው ብለዋል አምባሳደር ዲና።

እነዚህ ሦስት ነጥቦች "የድርድር ቅደመ ሁኔታዎች ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ" ያሉት አምባሳደር ዲና፤ በአሁኑ ወቅት በህወሓት እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል የተጀመረ ድርድር የለም ብለዋል።

አምባሳደር ዲና ሐሙስ ኅዳር 02/2014 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ድርድር አልተጀመረም፤ ስለ ድርድርም የተወሰነ ነገር የለም ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ሁልጊዜም የሰላም ፍላጎት እንዳለው የገለጹት አምባሳደር ዲና፤ "እንደ ደሃ አገር ለልማት ቅደሚያ እንሰጣለን" ብለዋል።

በትግራይ ክልል ውስጥ የተጀመረውና በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ እየተካሄደ ያለው ጦርነትም መንግሥት "ሳይፈልግ ተገዶ የገባበት" ነው ብለዋል።

የኦባሳንጆ ሽምግልና

የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት እና በቅርቡ የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት አሉሴጉን ኦባሳንጆ የፌደራሉን መንግሥት እና የህወሓት መሪዎችን አግኝተው ማነጋገራቸው ይታወሳል።

ኦባሳንጆ የፌደራል መንግሥቱን ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለማቀራረብ እያደረጉት ያለውን ሙከራ "ለማደራደር የማደርገውን ጥረት 'አልቀበልም' ያለ የለም" ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸው ነው።

አምባሳደር ዲና የኦባሳንጆን ተልዕኮ በተመለከተ፤ "ፋክት ፋይንዲንግ ሚሽን [ትክክለኛውን ዕውነት የመረዳት ተልዕኮ] ላይ ናቸው። ያሉትን ሁኔታዎች እየተመለከቱ ነው" ብለዋል።

አምባሳደሩ ኦባሳንጆ በአዲስ አበባ፣ በመቀለ፣ በሌሎች ክልሎች እና ከአፍሪካ ሕብረት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር እየተወያዩ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።

"በኢትዮጵያ በኩል ያለው አቋም ምንድነው ከተባለ፤ እኛ ለሰላም አዲስ አቋም የለንም" ካሉ በኋላ መንግሥታቸው ለሰላም መውረድ እክል የሚሆኑ ጉዳዮች የሚቀረፉበት መንገድ እንዲፈጠር ፍላጎት እንዳለው አመለክተዋል።

"ለሰላም እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች እስከተወገዱ ድረስ ወደ ሰላም የማንሄድበት ምክንያት የለም" በማለት የመንግሥታቸውን አቋም አሳውቀዋል።

አያይዘውም "የአፍሪካ ሕብረት መስራች ነን። የአፍሪካ ሕብረት ስሜትን እንቀበላለን። በአፍሪካ በኩል ችግር ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን ከምንም በላይ ቅድሚያ እንሰጣለን። ለዚህ ነው ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ እያልን ብዙ ጊዜ ስንደጋግም የነበረው። ስለዚህ ኦባሳንጆ ለምን መጡ? ለምን ሄዱ ልንል አንችልም" ብለዋል።

የተመድ ሠራተኞች እስር

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቅርቡ ሠራተኞቹ እና የሠራተኞቹ የቤተሰብ አባላት በአዲስ አበባ እና አፋር ውስጥ መታሰራቸውን ማስታወቁ ይታወሳል።

ተመድ ሠራተኞቹ ለምን እንደታሰሩ እና በአስቸኳይ እንዲፈቱ ለመንግሥት ጥያቄ ማቅረቡን ገልጿል። ይህንን በተመለከተ አምባሳደር ዲና በሰጡት ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን አስታውሰው፤ ሰዎቹም የታሰሩት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጣሳቸው መሆኑን ገልጸዋል።

"የተመድ ሠራተኛም ይሁን ማንም ሰው የኢትዮጵያን ሕግ የማክበር ግዴታ አለበት። ሕግ ካላከበር ማንም ይሁን ማን በሕግ ይጠየቃል። የታሰሩም ሰዎች አሉ። የታሰሩት ደግሞ የኢትዮጵያን ሕግ በመጣስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጣስ ነው" ብለዋል።