በደሴና ኮምቦልቻ መጋዘኖቹ በህወሓት ኃይሎች በመዘረፋቸው እርዳታ ማቋረጡን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ

እርዳታ የተሸከሙ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, WFP Ethiopia

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በአማራ ክልል በደሴና በኮምቦልቻ ከተሞች የነበሩት መጋዘኖቹ በህወሓት ኃይሎች በመዘረፋቸው በአካባቢዎቹ የምግብ እርዳታ ማቋረጡን አስታወቀ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ እንደተናገሩት የእርዳታ ምግብ ተከማችተውባቸው የነበሩት መጋዘኖቹ በአማጺያኑ በተዘረፉበት ወቅት በስፍራው በነበሩ ሠራተኞቹ መሳሪያ ተደግኖባቸው እንደነበረ አመልክተዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት እንደገለጸው በመጋዘኖቹ ላይ በአማጺያኑ በተፈጸመው ዝርፊያ በምግብ እጥረት ለተጎዱ ህጻናት የሚቀርቡ አልሚ ምግቦችን ጨምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው የምግብ አቅርቦት ክምችት ከሁለቱ ከተሞች ተወስደውበታል።

በስፍራዎቹ የነበሩ ሠራተኞቹም በጦር መሳሪያ ጭምር ጫናና ማስፈራሪያ ስለተደረሰባቸው ይህንን ዝርፊያ ለመከላከል ሳይችሉ መቅረታቸውም ተገልጿል።

ይህ ዝርፊያ በአሁኑ ወቅት ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በምግብ እርዳታ ላይ ጥገኛ በሆነበት በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የምግብ ዋስትና ችግርና የተመጣጠነ ምግብ እጦትን የበለጠ እንደሚያባብሰው ድርጅቱ ተናግሯል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ጨምሮም የመንግሥት ወታደሮች ሦስት የዓለም ምግብ ፕሮግራም የእርዳታ አቅራቢ ተሽከርካሪዎችን ለራሳቸው አገልግሎት ተጠቅመዋል ሲል ከሷል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘኖቹ መዘረፋቸውን ካሳወቀ ከአንድ ቀን በኋላ ህወሓት በሰጠው ምላሽ ኃይሎቹ የተባለውን ዘረፋ አለመፈጸማቸውን በማስተባበል ክሱን መሠረተቢስ በማለት አጣጥሎታል።

ለአንድ ወር ያህል በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር የቆዩት የደሴና የኮምቦልቻ ከተሞች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተመራው በክልልና በፌደራል ሠራዊት ጥምር ኃይል በተካሄደ ወታደራዊ ዘመቻ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከአማጺያኑ ነጻ መውጣታቸው ይታወሳል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት የኢትዮጵያ ሠራዊት በአፋርና በአማራ ክልሎች ውስጥ ባካሄደቻው ዘመቻዎች ቀደም ሲል በህወሓት ተዋጊዎች ቁጥጥር ስር የነበሩ በርካታ ስፍራዎችን መልሶ በቁጥጥሩ ስር አስገብቷል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 9.4 ሚሊዮን መድረሱን ከአንድ ሳምንት በፊት ማሳወቁ ይታወሳል።

ድርጅቱ በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኙት በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ወስጥ የሚገኙ 9.4 ሚሊዮን ሰዎች አስከፊ ሕይወት እየገፉ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ ከእነዚህ መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ማለትም 7.8 ሚሊዮን የሚሆኑት በጦርነቱ ምክንያት ሰብአዊ እርዳታ ማድረስ አዳጋች የሆኑባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎች ናቸው ብሎ ነበር።

የሰብአዊ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ለውጥ የታየው በአማራ ክልል መሆኑን ድርጅቱ አመልክቶ፤ በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል ውስጥ ብቻ 3.7 ሚሊዮን ሰዎች የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል።

ከትግራይ፣ ከአማራ እና ከአፋር የተሰበሰቡ መረጃዎች እንዳመለከቱት በሦስቱ ክልሎች ከሚገኙ ሕጻናት መካከል ከ16 እስከ 18 በመቶ የሚሆኑት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ነፍሰ ጡር ከሆኑ እና ከሚያጠቡ እናቶች መካከል 50 በመቶ ያህሉ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው መለየቱን እና ይህም የመንግሥታቱን ድርጅት በእጅጉ እንዳሰሰበው አመልክቷል።

በተጨማሪም የዓለም ምግብ ፕሮግራም በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በኢትዮጵያ ለሚያቀርበው ድጋፍ ከፍተኛ የገንዘብ ጉድለት እንዳጋጠመው ገልጿል።

በዚህም በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ድጋፎች ለሚደረግላቸው 12 ሚሊዮን ሰዎች ከሚያስፈልገው ገንዘብ የ579 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ጉድለት አጋጥሞታል።

ይህም በሰሜን ኢትዮጵያ ለ3.7 ሚሊዮን ሰዎች በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በአስቸኳይ ለሚያቀርባቸው የምግብና የአልሚ ምግቦች የሚውለውን 316 ሚሊዮን ዶላር ይጨምራል።