ጄፍሪ ፌልትማን ለሌላ ዙር ተልዕኮ ወደ አረብ ኤሜሬትስ፣ ቱርክ እና ግብፅ ያመራሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን
የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን በኢትዮጵያ ጉዳይ ለመምከር ወደ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ፣ ቱርክ እና ግብፅ ያመራሉ ተባለ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራስ ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ ፌልትማን ወደ ሦስቱ አገራት ጉዟቸውን የሚያደርጉት ከዛሬ ሐሙስ ኅዳር 30/2014 ዓ.ም ጀምሮ ነው።
"በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ግጭት ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና ደኅንነት ስጋት እንደሆነ እናውቃለን" ያሉት ኔድ ፕራይስ፤ አምባሳደር ፌልትማን ወደ አገራቱ ተጉዘው ከአጋሮች ጋር ውይይት ያደርጋሉ ብለዋል።
ቃል አቀባዩ፤ የአሜሪካ መንግሥት ለዚህ ግጭት ወታደራዊ እርምጃ መፍትሄው አይሆንም ብሎ እንደሚያምን አስታውሰው፤ የፌልትማን ተልዕኮም ግጭቱን ለማስቆም "ዲፕሎማሲን የመጀመሪያው፤ የመጨረሻው እና ብቸኛው አማራጭ" በማድረግ ተዋጊ ኃይሎች ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁመው ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ማስቻል ነው ብለዋል።
ፌልትማን ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት፤ የህወሓት አማጺያን ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞችን ተቆጣጥረው አዲስ አበባን የመያዝ ፍላጎት እንዳላቸው በሚገልጹበት ወቅት ነበር።
ፌልትማን ከሁለት ሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ የነበራቸው ጉብኝት አጠናቀው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ አላማ የህወሓት አማጺያንን ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች ማስወጣት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚንሰትሩ ኅዳር 12/2013 ዓ.ም. ላይ "ዋና አላማቸው የህወሓት አማጺያን ተቆጣጠረዋቸው ከሚገኙባቸው የአማራ እና አፋር ክልሎች ማስወጣት መሆኑን ነግረውኛል" ሲሉ አምባሳደር ፌልትማን ተናግረው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "የትግራይ መከላከያ ኃይልን ወደ ሰሜን ገፍቶ ወደ ትግራይ መመለስ እንደሚቻል ተማምነዋል። በዚህ መተማመን ላይ ግን ጥያቄ አለኝ። ሰኔ መጨረሻ ላይ የአገር መከላከያ ሠራዊት ትግራይን ለቅቆ ከወጣ በኋላ ስላለው ሁኔታ ካርታ ስመለከት በዚህ ዙሪያ ጥርጣሬ ያሳድርብኛል" ብለው ነበር ፌልትማን ከሁለት ሳምንታት በፊት።
ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሠራዊታቸውን ለመምራት ወደ ጦር ግንባር ማምራታቸውን ተከትሎ ባለፉት ሳምንታት በተካሄደ ወታደራዊ ዘመቻ በርካታ የአፋርና የአማራ ክልል አካባቢዎች ከአማጺያኑ ነጻ ወጥተዋል።
የህወሓት መሪዎች ግን ቀደም ሲል እዘዋቸው ከነበሩት አካባቢዎች የወጡት "በስልታዊ ውሳኔ" መሆኑን በመግለጽ ለሌላ ዘመቻ እተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የፌልትማን የቀጠናው ጉዞ
አምባሳደር ፌልትማን በኢትዮጵያ ጉዳይ ለመነጋገር በቀጠናው ወደሚገኙ አገራት ሲጓዙ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። አምባሳደሩ ከዚህ ቀደም ወደ አፍሪካ ቀንድ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ወደሚገኙ አገራት ጉዞ አድርገው ነበር።
ፌልትማን ከሚያዚያ 26 እስከ ግንቦር 4 2013 ዓ.ም. ባሉት ቀናት በኢትዮጵያ ጉዳይ ለመምከር ወደ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ኤርትራ እና ግብፅ አቅንተው ነበር።
ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ደግሞ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ስላሉ ጉዳዮችና እና በአፍሪካ ቀንድ የፀጥታ ሁኔታ ላይ ለመወያየት በሚል አምባሳደሩ ወደ ኳታር፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እና ኬንያ ተጉዘው ነበር።
ቱርክ፣ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ እና ግብፅ
ሦስቱ አገራት ከኢትዮጵያ እና ከአካባቢው አገራት ጋር የወዳጅነት እንዲሁም የፍጥጫ ግንኙነት እንዳለቸው የሚታወቅ ሲሆን በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በቀጠናው ሰላም ላይ ሚና እንዳለቸው ይታመናል።
ቱርክና ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዳላቸው የሚታወቅ ሲሆን በተለያዩ መስኮች እንደሚደጋገፉ በተደጋጋሚ የሚወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
ከዚህ አንጻር ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ግጭት ውስጥ የገቡት የህወሓት አመራሮች ቱርክ እና ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ለኢትዮጵያ መንግሥት ያቀርባሉ ሲሉ ይከሳሉ።
ምንም እንኳ ለዚህ ክስ ተጨባጭ መረጃ ባይታይም፤ የቱርክ መንግሥት ለኢትዮጵያ መንግሥት "የትኛውንም አይነት ድጋፍ ለማድረግ" ዝግጁ ነኝ ማለቱ ይታወሳል።
ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ነሐሴ 2013 በቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን በተደረገላቸው ግብዣ ወደ አንካራ አምርተው ከቱርክ መንግሥት ጋር ወታደራዊ እና የፋይናንስ ስምምነቶችን አድርገው ተመልሰዋል።
ፌልትማን በካይሮ በሚኖራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው እና ከግብፅ ጋር አለመግባባት ውስጥ ስለከተታት የሕዳሴ ግድብ እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ የፀጥታ ሁኔታ የመወያያ አጀንዳ ሊሆን ይችላል።