የአውስትራሊያው ምክትል ጠ/ሚ ለይፋዊ ጉብኝት ወደ ዩኬ አቅንተው በኮቪድ ተያዙ

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ባርናቢ ጆይስ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ,

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ባርናቢ ጆይስ

የአውስትራሊያው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ለይፋዊ ጉብኝት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም አቅንተው በኮቪድ መያዛቸው አሜሪካ በደረሱ ወቅት ተረጋገጠ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ባርናቢ ጆይስ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ጉብኝት ባደረጉት ወቅት በቫይረሱ ሳይያዙ እንዳልቀሩ ተናግረዋል።

አክለውም በአሁኑ ሰዓት እራሳቸውን ለይተው እንደሚገኙና ቀለል ያሉ ጉንፋን መሰል ምልክቶችን እንዳስተዋሉ ገልጸዋል።

ባርናቢ ጆይስ ረቡዕ ዕለት ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ከመጓዛቸው አስቀድመው በዩናይትድ ኪንግደም በነበራቸው ቆይታ የካቢኔ ሚኒስትር ከሆኑት ዶሚኒክ ራብ እና ግራንት ሻፕስ ጋር ተገናኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ እስካሁን ድረስ ለቫይረሱ ስርጭት ምን ያክል ስጋት እንደሆኑ አልታወቀም። እስካሁን ድረስ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር አብረው እየተጓዙ ካሉ የልዑክ ቡድን አባላት መካከል በቫይረሱ የተያዘ አልተገኘም።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሉት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ሲሄዱ ተመርምረው ኮሮናቫይረስ እንደሌለባቸው አረጋግጠው የነበረ ቢሆንም ልክ አሜሪካ ሲደርሱ ግን ድካምና እግራቸው አካባቢ የመዛል ስሜት አስተውለዋል።

ከዚህ በኋላ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለ10 ቀናት እራሳቸውን አግልለው እንደሚቆዩ የተገለጸ ሲሆን ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር ሊያደርጉት የነበረውም ውይይት ተሰርዟል።

ባርናቢ ጆይስ ከአውስትራሊያ መገናኛ ብዙኀን ጋር ባደረጉት ቆይታ ለገና በዓል ለንደን ውስጥ አንዳንድ እቃዎችን ለመግዛት ወደ ትልልቅ የገበያ ማዕከላት ማቅናታቸውን ያልደበቁ ሲሆን በርካታ ሰዎችም ትከሻ ለትከሻ ተጠጋግተው እንደነበር አስረድተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ከፍተኛ ስልጣን ላይ የሚገኙ የአውስትራሊያ ኃላፊ ናቸው።

የአውስትራሊያው መከላከያ ሚኒስትር ባሳለፍነው ዓመት ወደ አሜሪካ ጉዞ ካደረጉ በኋላ በቫይረሱ መያዛቸው የሚታወስ ነው።

አውስትራሊያ እስካሁን ድረስ በወረርሽኙ ምክንያት ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውን ያስታወቀች ሲሆን ይህም ካደጉት አገራት ጋር ሲነጻጸር በጣም ዝቅተኛ ቁጥር ነው።