አዲስ ምሩቅ የኬንያ ፖሊስ አባላት ያሰራጩት ቪዲዮ ቁጣን ቀሰቀሰ

የኬንያ ፖሊስ አባላት

የፎቶው ባለመብት, Twitter

አዲስ ምሩቅ የሆኑ የኬንያ ፖሊስ አባላት የሙያውን ሥነ-ምግባር ባልተከተለ መልኩ በተንቀሳቃሽ ምስል ሲዝቱ እና ሲያስፈራሩ መታየታቸው በኬንያውን ዘንድ ቁጣን ቀሰቀሰ።

አዲስ ምሩቅ የፖሊስ አባላቱ መልዕክቱን ካስተላለፉ በኋላ የአገሪቱ ፖሊስ ጉዳዩን አውግዞ ምርመራ አካሂዳለሁ ብሏል።

ተመራቂ ፖሊሶቹ በለቀቁት ተንቀሳቃሽ ምስል ስጋት የገባቸው ኬንያውያን ጉዳዩን ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ በማምጣት መወያያ አድርገውታል።

የአገሪቱ የፖሊስ ኃላፊዎች ጉዳዩን "ኃላፊነት የጎደለው፣ ተቀባይነት የሌለው እንዲሁም ቸልተኛ" ሲሉ ገልጸውታል።

ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ኬንያውያን የአገሬውን ፖሊስ እንደ ወንጀለኛ ቡድን ይመለከታሉ። ይህ የተለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስልም ይህንኑ እምነት የሚያጠናክር ሆኗል እየተባለ ነው።

ተመራቂ ፖሊሶቹ "በቃ ይሄው ነው፤ ጨርሰን ተመርቀናል። አሁን ወደ ውጪ ልንወጣ ነው። አደገኛ ሰዎች እኛ ነን። ቀይ መለዮ ለባሾች ፓ! ፓ! ፓ! ቡድን 26! እኛ ነን መጥፎዎቹ" ሲሉ ይታያል በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ።

ይህንን ተከትሎም በርካታ ኬንያውያን በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች በኩል ተንቀሳቃሽ ምስሉን ሲጋሩት ነበር። ጥቂት የማይባሉ ሰዎችም የኬንያ ፖሊሶች ሕዝቡን ከማገልገል ይልቅ ለራሳቸው ጥቅምና ሰዎችን ለማስፈራራት ነው የሚወጡት ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

አንዳንዶች ደግሞ ተመራቂ ፖሊሶቹ ወደ ሕዝቡ ሲቀላቀሉ ከንጹሃን ዜጎች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ኃይል ላይ የተመሰረተ እንደሚሆን ማሳያ ነው ብለዋል።

ይህ ተንቀሳቃሽ ምስል ይፋ የሆነው በኬንያ የፖሊስ ጭካኔ እና ተመጣጣኝ ያልሆኑ እርምጃዎች በተበራከቱበት እንዲሁም አገራዊ ምርጫ ወራት በቀሩበት ወቅት መሆኑ በርካቶችን አሳስቧል።

ኬንያ ውስጥ ፖሊሶች ኃይልን ያለአግባብ እንደሚጠቀሙ እንዲሁም አንዳንዴ ደግሞ እስከመግደል እንደሚደርሱ በተደጋጋሚ ይገለጻል። ነገር ግን ሥልጣናቸውን ያለአግባብ የሚጠቀሙት ፖሊሶች ለፍርድ ሲቀርቡ እምብዛም አይስተዋልም።

የኬንያ ብሔራዊ ፖሊስ ባወጣው መግለጫ ተንቀሳቃሽ ምስሉን በተመለከተ ምርምራ እየተደረገ እንደሆነና ተገቢው እርምጃም እንደሚወሰድ አስታውቋል።

አክሎም በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የተላለፈው መልዕክት ጠቅላላውን የፖሊስ ኃይል የማይወክልና ተቀባይነት የሌለው እንደሆነም ገልጿል።

በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ አካባቢ ደግሞ አንድ የኬንያ ፖሊስ አባል ባለቤቱን ጨምሮ ስድስት ሰዎችን ተኩሶ መግደሉ የሚታወስ ነው።

አሁን ደግሞ ይህ ተንቀሳቃሽ ምስል ይፋ መሆኑን ተከትሎ በርካታ ኬንያውያን 'ሊጠብቁን በተመደቡ ፖሊሶች እየተገደልን ነው' በማለት ተቃውሟቸውን እየገለጹ ነው።