ኢትዮጵያ አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያግዝ የምክክር ኮሚሸን ልታቋቁም ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister/fb

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሸን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ረቂቁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ መወሰኑን የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት አስታወቀ።

ሚኒስትሮች ምክር ቤት አርብ ታኅሣሥ 1 ቀን 2014 ባካሄደው ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባው ብልጽግና ፓርቲ ምርጫ አሸንፎ መንግሥት ሲመሰርት ለማከናወን ከወሰናቸው ተግባራት መካከል ኮሚሽኑን ማቋቋም እንደሚገኝበት ገልጿል።

በዚህም "ሁሉን አካታች የሆነ አገራዊ ምክክርና ውይይት በማካሄድ አገራዊ መግባባት እና በአገር ጉዳይ የጋራ አቋም እንዲኖር የሚያስችሉ ሥራዎችን መስራት አንዱ መሆኑ ይታወቃል" ይላል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የወጣው መግለጫ።

መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በተለያየ ጎራ የተሰለፉ ፖለቲከኞች እና ሕዝቡ ተቀራራቢ እና አንድነት ገንቢ አቋም እንዲይዙ ለማድረግ በገለልተኝነት ለመምራትና ለማስተባበር የሚችል ተቀባይነት ያለው ተቋም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነ ተገልጿል።

በዚህ መሠረትም የሚንስትሮች ምክር ቤት 'የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን' ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ለውሳኔ ቀርቦ ተቀባይነት በማግኘቱ ረቂቅ አዋጁ በቀጣይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ከጸደቀ ተፈጻሚነት ይኖረዋል።

ሐሙስ ዕለት ኅዳር 30/2014 ዓ.ም. የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውይይት ባደረገበት ወቅት በኢትዮጵያ የፖለቲካ የሽግግር ሂደት ተወያይቶ እንደነበረ የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

አደም ፋራህ ፓርቲው በውይይቱ አስፈላጊ ነው ያለው አገራዊው ምክክር ስኬታማ እንዲሆነ ገለልተኛ እና ብቃት ባለው ተቋም መመራት እንዳለበት ሥራ አስፈጻሚው አምኖበታል ስለማለታቸው ፋና ዘግቧል።