በነጮች ጥቃት ደረሰብኝ ያለው ሥመ ጥሩ ተዋናይ ለፖሊስ መዋሸቱ ተደረሰበት

ጀሲ ስሞልዬ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካዊው ዕውቅ ተዋናይ ጀሲ ስሞልዬ በማንነቴ የዘረኝነት ጥቃት ደርሶብኛል ሲል የተናገረው ሁሉ ነጭ ውሸት እንደነበር በፍርድ ቤት ተረጋገጠ፡፡

የቺካጎ ፍርድ ቤት በሰጠው ብይን የ39 ዓመቱ ተዋናይ ጀሲ፤ በጥቁርነቴና የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪነቴ ነጮች ጥቃት አደረሱብኝ ሲል ከዚህ ቀደም ያቀረበው አቤቱታ ሙሉ በሙሉ የተቀነባበረ የሐሰት ድራማ እንደነበረ ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡

ጥቃት እንደደረሰበት አድርጎ ድራማ ሠርቶ መላውን ዓለም ማታለሉን የቺካጎ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለሦስት ዓመታት ከተከታተለው በኋላ ደርሶበታል፡፡

በዚህ ድርጊቱም ተዋናዩ ጀሲ ጥፋተኛ ተብሎ ሐሙስ ዕለት ቅጣት ተጥሎበታል፡፡

ምንም እንኳ ሐሰት ለፖሊስ መናገርና በዚህ ደረጃ መዋሸት ሦስት ዓመት እስር ሊያስቀጣ የሚችል የነበረ ቢሆንም፤ የቺካጎ ፍርድ ቤት ሥመ ጥሩ ተዋናይ ከዚህ ቀደም በወንጀል ተጠያቂ ሆኖ ስለማያውቅ ቅጣቱን አቅልሎለታል፡፡

የቅጣት ማቅለያውን ተከትሎ ተዋናዩ በምንና እንዴት እንደሚቀጣ በቀጣይ ቀናት ይፋ ይሆናል ተብሏል፡፡

ጉዳዩን የተመለከተው የቺካጎ ፍርድ ቤት የዳኞች ጉባኤ 6 ወንዶችና 6 ሴቶችን ያካተተ ነበር፡፡ ይህ ጉዳይም ለወራት ከፍተኛ የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት የሳበ ጉዳይ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ሦስት ዓመት ፈጅቶበታል፡፡

እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ በጥር 2019 ነበር ለመጀመርያ ጊዜ ተዋናይ ጀሲ በማንነቴ ሰዎች ጥቃት ፈጸሙብኝ ብሎ የዓለም ዜና አውታሮችን በዜና ዕንባ ያራጨው፡፡

ዕውቁ ተዋናይ ጄሲ በዚያ ጊዜ ‹ኢምፓየር› በተሰኘ ተከታታይ ተወዳጅ ቴሌቪዥን ትዕይንት ቀዳሚ ተዋናይ ነበር፡፡

ጀሲ የተመሳሳይ ጾታ ወዳጅና ጥቁር በመሆኑና በነጮች ጥቃት ተፈጸመብኝ ማለቱ ጉዳዩ ከጥበብ ሰፈር አልፎ የፖለቲካ መንደሩን አዳርሶ በመላው አሜሪካና ካናዳ ሰፊ መነጋገሪያ ለመሆን በቅቶ ነበር፡፡

የያኔው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ድርጊቱን በይፋ አውግዘው ነበር፡፡

ጀሲ ያን ጊዜ ለፖሊስ በሰጠው ቃል በቺካጎ ጎዳና በሌሊት በሚሄድበት ሰዓት ሁለት ነጭ አክራሪዎች ይዘው ጸያፍ ስድብ እንደሰደቡት፣ በአንገቱ የገመድ ሸምቀቆ ሊያጠልቁበት እንደሞከሩና ያልታወቀ ውህድ ነገር ላዩ ላይ እንደደፉበት፣ ከዚያም ድብደባ አድርሰውበት እንደተሰወሩ በስሜት ሆኖ በየሚዲያው እየቀረበ ሲተርክ ነበር፡፡

ይህ የተናገረው ሁሉ ራሱ በራሱ ያቀነባበረው ድራማ እንደነበረ፣ ተዋናይ ጄሲም ሙልጭ ያለ ውሸት እንደዋሸ ፖሊስ መጠራጠር የጀመረው ምርመራውን በጀመረ በወራት ውስጥ ነው፡፡

ጀሲ ለምርመራው እንዲያግዝ የግል ተንቀሳቃሽ ስልኩን ለፖሊስ እንዲሰጥ ቢጠየቅም ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆነም ነበር፡፡

ይህም ሌላ ጥርጣሬን መፍጠሩ አልቀረም፡፡

ጀሲ ግን እንቢ ያልኩት በስልኬ ብዙ ምሥጢሮች ስላሉ ነው ሲል ነገሩን አስተባብሎ ነበር፡፡

በመጨረሻ ፖሊስ ተዋናዩ ራሱ ለሁለት ጭምብል ላጠለቁ ጥቁር ጓደኞቹ 3500 ዶላር በመክፈል ሆን ብሎ ጥቃት እንዲያደርሱበት ማድረጉን ደርሶበታል፡፡

ክፍያውን የፈጸመበት ቼክ እንደ ማስረጃ የቀረበ ሲሆን ሁለት ጥቁር ጓደኞቹም ጭምብል ሲገዙ የሚያሳይ የቁጥጥር ካሜራ ሰነድ ተገኝቷል፡፡

የጀሲን ጉዳይ በቅርብ የተከታተሉ የዝነኛ ሰዎች ጉዳይ ተንታኞች እንደሚጠረጥሩት ጀሲ ይህን ሁሉ ድራማ የፈጠረው ሥምና ዝናውን ይበልጥ ከፍ ለማድረግ በመቋመጡ ነው፡፡

በኢምፓየር የቴሌቪዥን ተከታታይ ትዕይንት የሚከፈለው ገንዘብ አነስተኛ እንደሆነም ሳት ብሎት ተናግሮ ነበር በወቅቱ፡፡

ጀሲ በዚያ ትዕይንት 100ሺህ ዶላር በምዕራፍ (ኢፒሶድ) ይከፈለው እንደነበር በጊዘው ይፋ አድርጎ ነበር፡፡