ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን ባለቤቱ አረጋገጠች

ታምራት

የፎቶው ባለመብት, Tamrat negera/fb

ተራራ ኔትወርክ የተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ መስራችና ዋና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ከመኖሪያ ቤቱ በፖሊስ ተይዞ መወሰዱን ባልደረቦቹና ባለቤቱ ለቢቢሲ ተናገሩ።

የቀድሞው የአዲስ ነገር ጋዜጣ ባልደረባ እንዲሁም ከስደት መልስ ተራራ ኔትወርክ የተሰኘው የዩትዩብ ሚዲያ ላይ ሲሰራ የቆየው ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ከመኖሪያ ቤቱ በፀጥታ ኃይሎች ተይዞ መወሰዱን ባለቤቱ ሰላም በላይ ለቢቢሲ ተናግራለች።

ታምራት ዛሬ ታኅሣሥ 01/2014 ዓ.ም ረፋድ ላይ ከመኖሪያ ቤቱ ምክንያቱ ሳይገለጽ ለጥያቄ እንደሚፈለግ ተነግሮት በፀጥታ ኃይሎች ወደ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዱን ባልደረቦቹም አረጋግጠዋል።

ባለቤቱ ለቢቢሲ እንደተናገረችው ወደ መኖሪያ ቤታቸው የመጡት ሲቪል የለበሱ እና ፖሊስ ነን ያሉ ግለሰቦች እንዲሁም መሳሪያ የታጠቁ የፌደራል ፖሊስ አባላት እንደነበሩና ወደ ሥራ ቦታውም እንደሄዱ አመልክታለች።

ከታምራት የሥራ ቦታ እንዲሁም ከመኖሪያ ቤቱ በርካታ ንብረቶችን የፀጥታ ኃይሎቹ ይዘው መሄዳቸውን የተናገረችው ሰላም "እስሩ ከሥራው ጋር የተገናኘ ሊሆን እንደሚችል ቀጥታ ወደ ሥራ ቦታው መሄዳቸውን በማየት አውቀናል። የፍርድ ቤት ወይም የተከሰሰበት ወረቀት የለም። ዝም ብለው ለጥያቄ እንፈልግሃለን ብለው ነው የወሰዱት" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ከቢሮው በኋላ የፀጥታ ኃይሎቹ ታምራትን በድጋሚ ወደ መኖሪያ ቤቱ ይዘውት ተመልሰው በመምጣት ለሁለተኛ ጊዜ ፍተሻ ማካሄዳቸውንም ባለቤቱ ገልጻ፣ ታምራት በምን ወንጀል እንደተጠረጠረ እንደማታውቅ እና "በመጨረሻም ልብስ ስጡት ብለው ይዘውት ሄዱ" ብላለች።

"ጠበቃ ይዘን እንድንመጣ በምን ወንጀል እንደተጠረጠረ ንገሩን ስንል 'እሱን ከምርመራ እና ከጥያቄ በኋላ ነው የምናውቀው። አሁን ምንም የምንላችሁ ነገር የለም። ለጥያቄ ነው የምንፈልገው' ብለው ሄዱ" ስትል ሰላም ለቢቢሲ ተናግራለች።

ቢቢሲ ታምራት ስለተጠረጠረበት ጉዳይ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካው ፈንታን ጠይቆ ኃላፊው ስለእስሩ የሚያውቁት ነገር እንደሌለና "አጣርተን ምላሽ እንሰጣለን" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ባለቤቱ ሰላም ታምራት በተለምዶ ሦስተኛ ተብሎ ወደሚጠራው የአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዱን ፖሊሶቹ እንደነገሯት እና ከዚያ ውጪ ግን በትክክል የት እንደሚገኝ በራሷ አለማረጋገጧን ገልጻለች።

ታምራት ነገራ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከመወሰዱ በፊት የፀጥታ ኃይሎች መኖሪያ ቤቱንና ቢሮውን በመፈተሽም ይፈለጋሉ ያሏቸውን ላፕቶፕ፣ ኮምፒውተሮች፣ መቅረፀ ድምፅ እና ሌሎች የተለያዩ ዕቃዎችን መውሰዳቸው ተነግሯል።

ታምራት ነገራ ከአስር ዓመት በፊት በህትመት ላይ ቆይታ ከፍተኛ ዝና አትርፋ በነበረችው የአዲስ ነገር ጋዜጣ ላይ ፖለቲካዊ ትንታኔዎችን በመጻፍ ይታወቅ የነበረ ሲሆን፣ ጋዜጣዋ በመንግሥት ጫና ስትዘጋ ታምራትን ጨምሮ አብዛኞቹ የአዲስ ነገር ባልደረቦች ለስደት መዳረጋቸው ይታወሳል።

ታምራት ነገራ ለዓመታት በአሜሪካ በስደት ከቆየ በኋላ በአገሪቱ ከሦስት ዓመት በፊት የመጣውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ ወደ አገር ቤት ተመልሶ ባለፈው ዓመት ተራራ ኔትወርክ የተባለውን የዩቲብ መድረክ በመጀመር የተለያዩ ይዘት ያላቸውን ፕሮግራሞች ሲያቀርብ ቆይቷል።

ከቀናት በፊት 'ኡቡንቱ' የተባለው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ባልደረባ እና አክቲቪስት እያስፔድ ተስፋዬ በተመሳሳይ ከቤቱ ተወስዶ መታሰሩን ቤተሰቦቹ ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።