ጁሊያን አሳንጅ ለአሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጥ ፍርድ ቤት ወሰነ

ጁሊያን አሳንጅ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የዊኪሊክስ መስራቹ ጁሊያን አሳንጅ ከዩናይትድ ኪንግደም ወደ አሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጥ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወስኗል።

በጥር ወር የዩናይትድ ኪንግደም ፍርድ ቤት አሳንጅ ከአዕምሮ ጤንነት ጋር በተያያዘ ተላልፎ እንዳይሰጥ ወስኖ የነበረ ቢሆንም አሜሪካ ጉዳዩን በይግባኝ ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በመውሰድ አሸንፋለች።

አሜሪካ አሳንጅ ራሱን የማጥፋት አደጋ ለመቀነስ ለዳኞች ቃል በመግባት አረጋግጣለች። ነገር ግን እጮኛው በበኩሏ ይህ ውሳኔ እንዲቀለበስ ይግባኝ ለማለት እንዳሰቡ ተናግራለች።

አሳንጅ በአውሮፓውያኑ 2010 እና 2011 በሺዎች የሚቆጠሩ ሚስጥራዊ ሰነዶችን ይፋ በማውጣትና በማተም በአሜሪካ በጥብቅ ይፈለጋል።

ከፍተኛ ዳኞች፣ የታችኛው ፍርድ ቤት ዳኛ አሳንጅ ተላልፎ ከተሰጠ በጣም ገዳቢ በሆኑ የእስር ቤቶች ውስጥ ሊታሰር ይችላል በሚል ስጋት ላይ ውሳኔያቸውን መሰረት እንዳደረጉ ተገንዝበዋል።

ነገር ግን፣ የአሜሪካ ባለስልጣናት ለወደፊቱ ተገቢውን ሁኔታ እስካሟላ ድረስ ገዳቢና ጥብቅ ቁጥጥር ባለበት እስር ቤት እንደማያስገቡት ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

በብያኔው ሰዓት የተናገሩት ሎርድ በርኔት "ሊገጥም የሚችለው አደጋ በተሰጠን ማረጋጋጫዎች ሊቀረፍ እንደሚችል ተረድተናል" ብለዋል።

"አሜሪካ በሰጠችን ዋስትና ረክተናል። ይህ ዋስትና ለቀድሞ ዳኛዋ ቀርቦ የነበረ ቢሆን ጥያቄውን በተለየ መንገድ ትመልስ ነበር" ብለዋል።

የአሳንጅ እጮኛ ስቴላ ሞሪስ በበኩሏ ብያኔውን "አደገኛ እና የተሳሳተ" ስትል የጠራችው ሲሆን የአሜሪካ ዋስትና ማረጋገጫዎች "አስተማማኝ አይደሉም" ስትል ተናግራለች።

ከፍርድ ቤቱ ውጭ በሰጠችው ስሜታዊ መግለጫ፣ ስቴላ "ባለፉት... ሁለት አመት ተኩል ጁሊያን በቤልማርሽ እስር ቤት ቆይቷል፣ እንዲያውም ከታህሳስ 2010 ጀምሮ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ለ11 ዓመታት ያህል ታግቶ ነው የቆየው። ይህ ለምን ያህል ጊዜ ሊቀጥል ይችላል?" ስትል ጠይቃለች።