የአሜሪካ የዋጋ ንረት በ40 አመታት ውስጥ ከፍተኛው ነው ተባለ

ፓትሪሺያ

አሜሪካውያን ሸማቾች በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው በአገሪቱ እየተከሰተ ያለው ከፍተኛ የዋጋ ንረት ከፍተኛ ጫና እያሳደረባቸው ነው፤ የዘንድሮው ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት ሁኔታም ለባለፉት አራት አስርት ዓመታት አልታየም።

የቅርብ ጊዜ አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የዋጋ ጭማሬው ከጥር እስ እስከ ህዳር ወራት ባለው ወቀት 6.8 በመቶ ደርሷል።

በሃርለም፣ ኒውዮርክ የፅዳት ሰራተኛ የሆነች ቢቢ የተባለች ግለሰብ በዋጋ ንረት ምክንያት በርካታ ወጪዎቿን መቀነስ ነበረባት ይህም ምግብን ይጨምራል።

አንዳንድ ጊዜም ከ27 አመት ልጇ ጋር አንድ ምግብ ብቻ ገዝተው እሷን ተካፍለው ይውላሉ፣ ያድራሉ።

"ምንም አማራጭ የለንም። ምግብ ለማብሰል አቅሙም የለኝም" ብላለች።

"ከገዛነው ምግብ ላይ ትንሽ እወስድና የበለጠውን ለሱ እሰጠዋለሁ ምክንያቱም እናት ሁልጊዜ ለልጇ እንዲሁ ነው የምታደርገው" በማለት ታስረዳለች።

የዋጋ ንረት በተለይም ምግብና ሸቀጦች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የታየ ሲሆን የነዳጅ ዋጋ 6.1 በመቶ ጨምሯል፣ መኪናዎች እና የቤት ኪራይ ዋጋም እንዲሁ ከፍተኛ መናር አሳይተዋል።

ወርሃዊ የዋጋ ጭማሬው ከጥቅምት ወር 0.9 በመቶ ሲነፃፀር በተወሰነ መልኩ ቅናሽ ያሳየ ሲሆን ሆኖም የህዳር ወር 0.8 በመቶ እንደነ ቢቢ ላሉ ሰዎች በአጠቃላይ ካለው ገቢያቸው ምንም መሻሻል ባለመኖሩ ጫናው አልቀለለም።

የቢቢሲ ጋዜጠኛ በአንድ ትልቅ መደብር ያገኛት ፓትሪሺያ በየሳምንቱ ለምግብ የምታወጣው ወጪ በ30 ዶላር ያህል ከቀድሞው ከፍ እንዳለ ገልጻ ስትገዛው የነበረውን የዶሮና የአሳማ ስጋን በአትክልቶች መተካቷን ትናገራለች። የአትክልቶች ዋጋም ውድ ቢሆን የተሻለ ነው ትላለች።

"ዳፋው በጣም ከፍተኛ ነው ስራም እየሰራሁ አይደለም" ትላለች።

በቅርቡ ጡረታ የወጣችው ፓትሪሺያ በዋነኝነት የምትገዛው ሸቀጥ በጣም መወደድ ብቻ ሳይሆን የመጠኑንም ማነስ አስተውላለች በተለይም በጣፋጭ የተለወሰ ዳቦ።

"ከአሁን በኋላ ብዙም እንደማልገዛቸው ተረድቻለሁ። ቀድሞ ትልልቅ ነበሩ። በአሁኑ ወቅት ውድና ትንንሽ ሆነዋል" ትላለች።

ከአውሮፓውያኑ 1982 ጀምሮ የዋጋ ግሽበት በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሬ እያሳየ ይገኛል።

ነገር ግን ከፍተኛ ተፅዕኖውና ዳፋው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸውና ገንዘባቸውን በበቂ ሁኔታ ማመጣጠን ባልቻሉት ላይ አሜሪካውያን ዘንድ ነው።

እየጨመረ የመጣው የዋጋ ግሽበት በፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር ላይ ጫናን የፈጠረ ሲሆን ይህንንም ሁኔታ ለማቃለልና እፎይታ ለመፍጠር የ1.9 ትሪሊየን ማህበራዊ ወጪ ፕሮግራምንም ነድፈዋል።

አንዳንድ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በበኩላቸው የዋጋ ጭማሪን በማባባስ በኮቪድ ወረርሽኙ መካከል ድጋፍ ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀው የፕሬዚዳንቱ የቀድሞ የወጪ መርሃ ግብሮችን ይጠቅሳሉ።