የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ በኮቪድ ተያዙ

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚደንት ሲይሪል እንደ አውሮፓውያኑ 2017 ከእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስተር ቴሬዛ ሜይ ባደረጉት ስብሰባ ወቅት መንገዶችን ለመቀነስ መግለጫ ሰጥተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ኮቪድ-19 ፖዘቲቭ እንደሆኑ ጽህፈት ቤታቸው ትላንት ምሽት ይፋ አድርጓል።

እሑድ ዕለት በኮቪድ መያዛቸው የተገለጠው ራማፎሳ መካከለኛ የሕመም ስሜት እንዳላቸው የአገሪቱ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት በትዊተር ገፁ ላይ አስፍሯል።

ፕሬዝደንቱ የሕመም ስሜት ይሰማቸው የጀመረው የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዝደንት ዴ ክላርክ መታሰቢያ ዝግጅት ላይ ለመገኘት ከመንቀሳቀሳቸው በፊት መሆኑም ታውቋል።

በቅርቡ በሞት የተለዩት የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዝደንት ዴ ክላርክ የአገሪቱ የመጨረሻው ነጭ መሪ ነበሩ።

ራማፎሳ ኮቪድ-19 እንደያዛቸው ከታወቀ በኋላ በደቡብ አፍሪካ መከላከያ ሠራዊት ወታደራዊ የጤና አገልግሎት ዶክተሮች ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ ቢሯቸው አሳውቋል።

"ጥሩ ተነቃቅተዋል" ብሏል የፕሬዝደንቱን በኮቪድ መያዝና ተያያዥ ጉዳዮችን በትዊተር ገፁ ያሰፈረው ጽ/ቤታቸው።

ሙሉ ክትባት የወሰዱት ራማፎሳ ኬፕ ታውን ውስጥ ራሳቸውን አግልለው የተቀመጡ ሲሆን የመሪነት ኃላፊነቱን ምክትላቸው ዳቪድ ማቡዛ ተረክበዋል።

በቅርቡ ወደ ምዕራባዊ የአፍሪካ አገራት ጉዞ ያደረጉት ራማፎሳ በሄዱበት ሁሉ እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ የሥራ አጋሮቻቸውም የኮቪድ ምርመራ አድርገው እንደነበር ተገልጧል።

ራማፎሳ ባለፈው ረቡዕ ለኦፊሴላዊ የሥራ ጉብኝት ካመሩባት ሴኔጋል ተመልሰው ወደ ጆሃንስበርግ ሲመጡ በሙሉ ጤንነት ላይ ነበሩ።

ፕሬዝደንቱ "የኔ በበሽታው መያዝ ለደቡብ አፍሪካዊያን ትምህርት እንዲሆንና እንዲከተቡ እፈልጋለሁ" ብለዋል ብሏል ጽህፈት ቤታቸው።

ከፕሬዝደንቱ ጋር ንክኪ የነበራቸው ሰዎች ራሳቸውን አግልለው የበሽታውን ምልክቶች በጥንቃቄ እንዲያጤኑ ጽ/ቤታቸው ትዕዛዝ አስተላልፏል።

የደቡብ አፍሪካ ሳይንቲስቶች በቅርቡ ኦሚክሮን የተሰኘውን ዝርያ አግኝተው ለዓለም ሕዝብ ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም።

ወደ አራተኛው የበሽታው ማዕበል እየተጓዘች ባለችው ደቡብ አፍሪካ ኦሚክሮን የተሰኘው አዲስ የኮቪድ ዝርያ በመገኘቱ ምክንያት በበርካታ አገራት የጉዞ ጥቁር መዝገብ ላይ ሰፍራለች።

በወቅቱ ፕሬዝደንት ራማፎሳ ዶክተሮቻቸው አዲሱን ዝርያ ፈልገው በማግኘታቸው በጉዞ ዕግድ ላይ ደቡብ አፍሪካ መስፈሯ ትክክል አይደለም ሲሉ ተናግረው ነበር።