በአሜሪካው ከባድ አውሎ ነፋስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካዋ ኬንታኪ ውስጥ የሚገኙ ከተሞችን ካወደመው ተከታታይ ከባድ አውሎ ነፋስ በሕይወት የተረፉ ሰዎችን የማግኘቱ ተስፋ በመመናመኑ በአደጋው የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ100 በላይ ሊሆን እንደሚችል የግዛቲቱ ገዢ ተናገሩ።
እስካሁን ሰማኒያ ሰዎች መሞታቸው የተረጋገጠበት ከባድ አውሎ ነፋስ በአውዳሚነቱ በኬንታኪ ግዛት ታሪክ ውስጥ ካጋጠሙት ከባዱ እንደሆነ አስተዳዳሪው ኤንዲ ቤሼር ተናግረዋል።
ይህ የተፈጥሮ አደጋ በተከሰተባቸው አካባቢዎች አብዛኛው ነገር የፈራረሰ ሲሆን ከኬንታኪ በተጨማሪ በሌሎች አራት የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ 14 ሰዎች በአውሎ ነፋሱ ሳቢያ ለሞት መዳረጋቸው ተዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጉዳቱን ተከትሎ በኬንታኪ ግዛት ውስጥ ከባድ አደጋ መድረሱን ያወጁ ሲሆን በአውሎ ነፋሱ ክፉኛ በተጎዱ አካባቢዎች የፌደራል መንግሥቱ እርዳታ እንዲያቀርብ አዘዋል።
የእርዳታ ሠራተኞች ለነዋሪዎች ውሃና ጄኔሬተሮችን እያቀረቡ ሲሆን የነፍስ አድን ሠራተኞች ደግሞ በፍርስራሾች ስር ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን ለማግኘት ፍላጋ ላይ ናቸው። ከ300 በላይ የብሔራዊ ዘብ አባላት ከቤት ቤት እየተዘዋወሩ ፍርስራሾችን እያነሱ ይገኛሉ።
"ፍለጋችንን በቀጠልን ቁጥር በተዓምር ተጨማሪ በሕይወት ያሉ ሰዎችን እንደምናገኝ ተስፋ እናደርጋለን" በማለት የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ከባድ ጉዳት የደረሰባትን ሜይፊልድ የተባለችውን ከተማ በጎበኙበት ጊዜ ተናግረው ነበር።
ነገር ግን ከቅዳሜ ጠዋት ወዲህ ባለፉት ሁለት ቀናት በተደረጉ ፍለጋዎች በሕይወት የተገኙ ሰዎች የሉም።
አውሎ ነፋሱ ሰፊ ቦታዎችን በመምታቱ ከባድ ጉዳትን አድርሷል። እስካሁን ትክክለኛው ቁጥር ባይታወቅም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአደጋው መኖሪያቸው ወድሟል።
በከተሞቹ ያሉ ትልልቅ ተቋማት የፈረሱ ሲሆን 110 ሠራተኞች በነበሩበት በአንድ የሻማ ፋብሪካ ላይ በደረሰ ጉዳት ስምንት ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች ስምንት ሠራተኞች እስካሁን እንዳልተገኙ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ለሮይተርስ ዜና ወኪል ተናግሯል።
በኤሊኖይ ግዛት ውስጥ የሚገኝ አንድ የአማዞን መጋዘን በከባዱ አውሎ ነፋስ በመፍረሱ ስድስት ሰዎች ሲሞቱ በርካታ ሰዎች ደግሞ እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም።
ቴኒሲ ውስጥ አራት ሰዎች፣ በአርካንሳስ ሁለት እንዲሁም ሚዙሪ ግዛት ውስጥ ደግሞ አንድ ሰው በአደጋው ለህልፈት ተዳርገዋል።
ይህንን ከባድ አውሎ ነፋስ ተከትሎ ፕሬዝዳንት ባይደን የአገሪቱ የአካባቢ ጥበቃ መሥሪያ ቤት የአየር ጠባይ ለደረሰው አደጋ ምን አስተዋጽኦ እንዳለው ምርመራ እንዲያደርግ ጥያቄ አቀርበዋል።