የሩሲያ ፍንዳታ: አንድ ታዳጊ በኦርቶዶክስ ትምህርት ቤት ውስጥ ፍንዳታ ማድረሱ ተገለጸ

ትምህርት ቤት

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ,

ፍንዳታው ከደረሰበት የሰርፑክሆቭ ትምህርት ቤት የተመረቀው የ18 ዓመት ወጣት ራሱን ለማጥፋት ሞክሯል።

አንድ ሩሲያዊ ታዳጊ ከሞስኮ ወጣ ብሎ በሚገኝ ገዳም አቅራቢያ ባለ የኦርቶዶክስ ትምህርት ቤት ፈንጂ በማፈንዳት በርካታ ሰዎችን አቆሰለ።

የሩሲያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው ፍንዳታው ከደረሰበት የሰርፑክሆቭ ትምህርት ቤት የተመረቀው የ18 ዓመት ወጣት ራሱን ለማጥፋት ሞክሯል። ሆኖም ሕይወቱ መትረፉ ተገልጿል።

ሚኒስቴሩ እንደገለጸው ከቆሰሉት መካከል የ15 ዓመት ታዳጊ ይገኝበታል። የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን እስከ 12 የሚደርሱ ሰዎች ተጎድተዋል ብለዋል።

በሩሲያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ታዳጊ ወጣቶች በትምህርት ቤቶች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት እየጨመረ ይገኛል።

ፈንጂውን ያፈነዳው ታዳጊ በሕይወት ቢተርፍም በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በሆስፒታል እንደሚገኝ መገናኛ ብዙኃኑ እየዘገቡ ነው። የታዳጊውን ስም ግን አልጠቀሱም።

የሩሲያው የዜና ወኪል ኢንተርፋክስ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ታዳጊው በትምህርት ቤቱ መምህራን እና ተማሪዎች ላይ ያለው ጥላቻ ለጥቃቱ ሳያነሳሳው አልቀረም ብሏል።

ታስ የተባለው የዜና ወኪል በበኩሉ የቀድሞው የሁለተኛ ደረጃ ትህምርት ቤቱ ተማሪ በጧት ጸሎት ወቅት ጥቃት ለመሰንዘር ቢያቅድም ፍንዳታው የደረሰው ግን በገዳሙ መግቢያ ላይ መሆኑን ገልጿል።

በሞስኮ ያለ ዐቃቤ ሕግ የግድያ ሙከራ መዝገብ ቢከፍትም የጥቃቱ ምክንያት ግን እስካሁን በይፋ አልተረጋገጠም ።

ዐቃቤ ሕግ ከገዳሙ ውጭ ፖሊስ እና አምቡላንሶችን የሚያሳይ ቪዲዮ ከሥፍራው ለቋል።

የሞስኮ አገረ ገዥ አንድሬ ቮሮብዬቭ ምን ያህል ተማሪዎች እንደተጎዱ ባይገልጹም አንዳቸውም ለሕይወት አስጊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንዳልሆኑ ተናግረዋል።

በቴሌግራም ባስተላለፉት መልዕክት "ሁሉም ሙያተኞች በሰዓቱ ምላሽ ሰጥተዋል። ዶክተሮች የተጎዱ ህጻናትን ረድተዋል" ብለዋል።

በሰርፑክሆቭ የሚገኘው የቬደንስኪ ቭላድይቺኒ ገዳም የተመሰረተው እአአ በ1360 ነው። ከሰባት እስከ 16 ዕድሜ መካከል ያሉ ህጻናት ከሞስኮ በስተደቡብ 100 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው ትምህርት ቤት ይማራሉ።

የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተጎጂዎችን ለመርዳት ቃል ገብታለች።

በሩሲያ ውስጥ በሐይማኖታዊ ተቋማት ላይ የሚከሰቱ ክስተቶች እምብዛም አይደሉም። ሆኖም አገሪቱ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በትምህርት ቤቶች ላይ በታዳጊዎች የሚደርሱ ጥቃቶች እየጨመሩ መጥተዋል።