ወሎ ላሊበላ ኪነት ፡ ሕይወቷ አልፎ የተገኘችው የመሰንቆዋ ንግሥት ፈንታየ ተሰማ ማን ነበረች?

የመሰንቆዋ ንግሥት ፈንታየ ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, Werebabo Culture and Tourism/ Atronos Media

የፈንታየ እና የመሰንቆ ትውውቅ የጀመረው ከልጅነት ነው። ቅርበታቸውም የእናትና ልጅ ያህል ነው። መሰንቆዋን ይዛ ያልሄደችበት የኢትዮጵያ ጫፍ የለም። አምባሰል፣ ባቲ፣ አንቺ ሆዬ፣ ትዝታን በመሰንቆዋ ተቀኝታቸዋለች።

ብዙዎች በኢትዮጵያ መሰንቆ የጨበጠች "የመጀመሪያዋ ሴት ናት" ይሏታል። እርሷ ግን "ሰዎች ይሉኛል፤ እኔ ግን የመጀመሪያ ስለመሆኔ አላውቅም" ነበር መልሷ።

በእርግጥ አሁን አሁን ባህላዊውን የክር የሙዚቃ መሣሪያ መሰንቆን፣ የሚማሩ በርካታ ሴቶች ቢኖሩም፤ ፈንታየ መሰንቆዋን ይዛ በወጣችበት ዘመን፤ መሰንቆን ማንሳት እንኳን ለሴቶች ለወንዶችም ቀላል አልነበረም። በማኅበረሰቡ እንደ ነውርም ይታይ ነበር።

ፈንታየ ግን ይህ ሁሉ አልበገራትም። ከልጅነት እስከ እውቀት ለሙያዋ ስትል ውጣ ውረዶችን አሳልፋለች።

አሁን ግን የምትወደውን መሰንቆዋን ጥላ ላትመለስ ተሰናብታለች።

ከወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድን መስራቾች አንዷ የሆነችው ፈንታየ ተሰማ የህወሓት አማጺያን ደሴ ከተማን ተቆጣጥረው በነበረበት ወቅት ቤቷ ውስጥ ሕይወቷ አልፎ መገኘቷን የደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ሶለሂማን እሸቱ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ፈንታየ ሕይወቷ መቼ እንዳለፈ በትክክል እንዳላወቁ ገልጸው፣ ደሴ ከተማ ከአማጺያኑ ነጻ ከመውጣቷ ሦስት ቀናት በፊት ሳትሞት እንዳልቀረች የዓይን እማኞችን ጠቅሰው ተናግረዋል።

ስለአማሟቷ ሁኔታም ፖሊስ ምርመራ መጀመሩን ኃላፊው ተናግረዋል።

'የመጀመሪያዋ' ሴት የመሰንቆ ተጨዋች ፈንታየ ማን ነበረች?

ፋንታየ ትውልዷ በቀድሞው አምባሰል አውራጃ፣ ቢስቲማ ወረዳ፣ ጭርቾ በሚባል መንደር ነው። ለቤተሰቦቿ ብቸኛ ልጅ ነበረች። አባቷ አቶ ተሰማ ኃይሉ ጎበዝ የመሰንቆ ተጨዋች ነበሩ።

እርሳቸውን እያየች ነው ያደገችው። ፈንታየ የአባቷ የመሰንቆ አጨዋወት ቀልቧን ይስበው ነበር።

አባቷ አቶ ተሰማ መሰንቆን የሚጫወቱት ለገቢ ማስገኛ፣ አሊያም ለመተዳደሪያ አልነበረም። ጎበዝ አርሶ አደር ነበሩ። መሰንቆን የሚጫወቱት ለግል ስሜታቸው እንደነበር እና መሰንቆ ሲጫወቱ ተከፍሏቸው እንደማያውቅም ፈንታየ ከዓመታት በፊት ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ በሰጠችው ቃለ ምልልስ ተናግራለች።

በመሰንቆ ፍቅር የወደቀችው ፈንታየ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለች ትምህርቷን አቋርጣ መሰንቆ አነሳች።

ለቤተሰቦቿ ብቸኛ ልጅ ስለነበረች ፍላጎቷን እምብዛም አልተጋፏትም።

በዚያን ወቅት ሴት ልጅ አግብታ፣ ልጅ ወልዳ ማሳደግ እንጂ በወንዶች የተለመደውን መሰንቆ ማንሳት የሚያሰድብ እንጂ የሚያስሞግስ አልነበረም እና የአካባቢው ማኅበረሰብ አባቷን ደጋግመው "ይችን ልጅ እንዲሁ ልታስቀራት ነው እያሉ. . ." እንዲያስተዋት ይወተውቷቸው ነበር።

እርሳቸው ግን "እርሷ ብቸኛ ልጄ ናት። ተዋት! ደስ ካላት የምትፈልገውን ትሁን " ነበር መልሳቸው።

መሰንቆን 'ሀ' ብላ የተማረችውም ከአባቷ ነው።

በዚህ ሁሉ መሃል ወላጆቿን በተከታታይ በሞት አጣቻቸው።

በሐዘን ልቧ የተሰበረው ፈንታየ መሰንቆዋን ብቻ አንጠልጥላ ያደገችበትን ቤት፣ የቦረቀችበትን መንደር ጥላ ወጣች።

"እናቴ በሞተች በሦስተኛ ቀኗ ነው አካባቢውን ለቅቄ የወጣሁት" ስትልም ተናግራለች። ያመራችውም ወደ አፋር አሳይታ ከተማ ነበር።

ከደሴ 300 ኪሎ ሜትር ገደማ በምትርቀው አሳይታ ከተማ በምሽት ቤቶች እየተዘዋወረች መሰንቆ መጫወት ጀመረች። 'ሴት ነኝ' ብላ በወቅቱ በነበረው የማኅበረሰቡ አመለካከት ሳትሸማቀቅ በድፍረት ትጫወት ነበር።

በዚህም በርካታ አድናቂዎችን መሳብ ችላ ነበር። ወደ የወሎ ላሊበላ ኪነት ለመግባት መንገድ የሆናትም ይኸው ዝናዋ ነበር።

ፈንታየና የወሎ ላሊበላ ኪነት እንዴት ተዋወቁ?

ይህ የሆነው ፈንታየ ከመሰንቆዋ ጋር አሳይታ ከከተመች ከአምስት ዓመታት በኋላ ነው።

በወቅቱ የወሎ ላሊበላ ኪነት አሰልጣኝ ሆነው የተመደቡት አርቲስት ቀለመወርቅ ደበበ ከአምባሰሏ ንግሥት ማሪቱ ለገሰ ጋር ወደ አሳይታ ለሥራ ጉዳይ ያመራሉ።

ምሽቱንም በጨዋታ ለማሳለፍ ወደ አንድ እውቅ ጠጅ ቤት ጎራ ባሉበት ነበር ፈንታየ መሰንቆዋን እየተጫወተች ያገኟት። ያኔ ዝናዋ በድፍን አሳይታ ከተማ ናኝቶ ነበር።

ከዚያም በአርቲስት ቀለመወርቅ አማካኝነት በ1971 ዓ.ም ወደ ደሴ ከተማ በመሄድ በ185 ብር ገደማ ደመወዝ ተቀጥራ ወሎ ላሊበላ የኪነት ቡድንን ተቀላቀለች።

እዚያም ከእነ ማሪቱ ለገሰ፣ ዚነት ሙሃባ፣ ዙሪያሽ አብዩ፣ ዘነበች እሸቴ፣ ዳምጤ መኮንን፣ መሐመድ ይመር (ከመከም)፣ አራጌ ይማም እና ሌሎችም ጋር ሠርታለች።

ከወንድ የባህል ሙዚቃ መሣሪያ ተጨዋቾች ጋር ተሰይማም በሄደችበት ሁሉ የመድረኩ ድምቀት ሆናለች- ፈንታየ ተሰማ።

"ብዙም ባልተለመደበት ዘመን ከወንዶቹ ጎን እኩል ተሰልፌ በመጫወቴ እጅግ ደስ ይለኝ ነበር" ብላለች ለአንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም በሰጠችው ቃለ ምልልስ።

ፈጣን ነው ባቡሩ ፣ ቃሮየ፣ እሪኩም፣ ከመከም፣ የተሰኙ የወሎ ባህላዊ ሙዚቃዎችን በመሰንቆ አጅባለች። የመድረክ ፕሮግራሞች ባሉበትም አትጠፋም። ያልሄደችበት፣ የመሰንቆ ጥበቧን ያላሳየችበት የኢትዮጵያ ክፍለ አገርም አልነበረም። ድንበር ተሻግራም በሱዳንና በኮሪያ በርካቶችን አስደምማለች።

ከዚያ ግን ከመሰንቆዋ ጋር የሚያፋታት አንድ አጋጣሚ ተከሰተ።

"በ1983 ዓ.ም ኢህአዴግ ሲገባ ምክንያቱን ሳናውቀው በአንዲት ብጣሽ ወረቀት የኪነት ቡድኑ ተበተነ፤ ከዛሬ ጀምሮ ተበትኗል ተባለ" ትላለች የተፈጠረውን ስታስታውስ።

በወቅቱ የኪነት ቡድኑ እንዲበተን የተደረገው "የቀድሞ ሥርዓት ደጋፊ ናችሁ" በሚል እንደሆነ ይነገራል።

በዚህ ሁኔታም አንጋፋ የሙዚቃ ባለሙያዎችን ያፈራው የጥበበኞች ስብስብ - ወሎ ላሊበላ ኪነት እንደዋዛ ተበተነ።

"መሰንቆየን ሰቀልኩ . . ."

የኢህአዴግን ሥልጣን መቆጣጠር ተከትሎ የተበተነው የኪነት ቡድን በሼህ ሁሴን አሊ አላሙዲን ድጋፍ እንደገና ተሰባሰበ። ሆኖም ብዙም አልተራመደም።

ለሰባት ወራት ያህል ከሰሩ በኋላ አሁንም የባህል ቡድኑ አባላት ከሥራ ታገዱ።

ፈንታየ "ምክንያቱን በውል በማላውቀው መንገድ "ላልተወሰነ ጊዜ ከሥራ ታግዳችኋል" በሚል በድጋሜ ቡድኑ ተበተነ ብላለች ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ በሰጠችው ቃለ ምልልስ።

ከዚያ ሸበሌ ሆቴል እና በማሪቱ ለገሰ አዲስ አበባ ምሽት ቤት ለተወሰነ ጊዜ ከሰራች በኋላ ማሪቱም ምሽት ቤቷን ዘግታ ወደ አሜሪካ በመሄዷ፣ አማራጭ ያልነበራት ፈንታየ ወደ የቀን ሥራ ገባች።

ሥራዋን ከመጀመሯ በፊት ግን ለአሰሪዎቿ የሙዚቃ አልበሟን እንዲያስቀምጡላት በአደራ ሰጥታቸው እንደነበርና አሰሪዎቿ አልበሟን ሲያገላብጡ ከኪነት ቡድኑ ጋር ያላትን ፎቶ አይተው ወደ ስቶር ሥራ እንዳስገቧት ለጋዜጣው ተናግራለች።

ወደዚህ የሥራ ክፍል የተዘዋወረችው ግን ሁለት ዓመታትን ድንጋይ በመሸከም ከሰራች በኋላ ነበር።

በወቅቱ ከእርሷ ጋር ይሰሩ የነበሩት የቡድኑ አባላት አብዛኞቹ በሞት በመለየታቸው ከእርሷ አጨዋወት ጋር ተቀናጅቶ የሚሰራ ባለሙያ አላገኝም በማለት ነበር ሌሎች የባህል ምሽት ቤቶች ውስጥ መስራትን ያልመረጠችው።

"ያኔ ፍላጎቴ መደበቅ ነበር። እኔ ለመሰንቆየ ክብር እሰጣለሁ። ብር ለማግኘት ከማይሆን ባለሙያ ጋር ከምሰራ ብዬ ነው ወደ የቀን ሥራ የገባሁት" ብላለች።

ወሎ ላሊበላ ኪነት እንደገና . . .

በ2005 ዓ.ም የወሎ ላሊበላ ኪነት እንደገና ተደራጀ። ያኔ እርሷ የት እንዳለች የሚያውቅ አልነበረም። 21 ዓመታት እንደዋዛ ነጉደዋል። መሰንቆዋም ለዓመታት ከተሰቀለበት አልወረደም።

ፈንታየ የት እንዳለች የታወቀው በአጋጣሚ ለአንድ ራዲዮ ጣቢያ በሰጠችው ቃለ መጠይቅ አማካኝነት ነበር።

በእርግጥ አብዛኞቹ የኪነት ቡድኑ አባላት በሞት ተለይተዋል። ማሪቱ ለገሰም አሜሪካ ገብታለች።

ቢሆንም ደስታዋ ወደር አልነበረውም። በሕዝቡም ደማቅ አቀባበል ነበር የተደረገላት። ነፍሷ ወደምትወደው ሥራዋ ተመለሰች። የምትወደውን መሰንቆም ከዓመታት በኋላ ዳግም አነሳች።

በወቅቱ ከነበረው የባህል ቡድኑ ስብስብ ውስጥ ግን ያገኘቻቸው መሐመድ ይመር (ከመከም) እና አራጌ ይማምን ብቻ ነበር።

አሁን እርሷ እና አራጌ ይማም ይህችን ዓለም ተሰናብተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Arts TV

የአንጋፋው መሰንቆ ተጨዋች አራጌ ይማምም ሕይወት ያለፈው ልክ እንደ ፋንታየ ሁሉ የደሴ ከተማ በህወሓት ቁጥጥር ሥር በነበረችበት ወቅት ነበር።

አራጌ ይማም አማጺያኑ በከተማዋ ሲያሽረክሩት በነበረ 'ኦራል መኪና' ተገጭተው ሕይወታቸው ማለፉንና በዚሁ አደጋ ሌሎች ሰዎችም መሞታቸውን ከዓይን እማኞች መስማታቸውን አቶ ሶለሂማን ገልጸውልናል።

አማሟታቸውን በተመለከተም ፖሊስ እና የባህልና ቱሪዝም መምሪያው በትኩረት ተከታትሎ እንደሚያሳውቅ ተናግረዋል።

ትንሽ ስለየወሎ ላሊበላ ኪነት

የወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድን መነሻ በ1960ዎቹ በደሴ ከተማ ምሽት ቤቶች የሚዘፍኑ አዝማሪዎች ነበሩ።

እነዚህ የባህልና ሙዚቃ ወዳጆችም ቁጥራቸው በርከት ይል ነበርና ተሰባስበው በ1964 ዓ.ም 'የወሎ ክፍለ አገር ባህል ተጨዋቾች ማኅበር' ን መሰረቱ።

ማኅበሩን ከሚመሩት መካከል መሐመድ ይመር (ከመከም) አንዱ ነበር።

አዝማሪዎቹ በጋራ በመስራት፣ ተመሳሳይ የሥራ ልብሶችን በማስፋት ሙያቸውን ተወዳጅ ለማድረግ ይተጉ ነበር።

ከዚያም በኢትዮ-ሶማሌ ጦርነት ወቅት በጂግጂጋ በተዘጋጀው የመልሶ ማቋቋም አገርህን እወቅ ባዛር ፕሮግራም ላይ ማኅበሩ ተጋብዞ ሥራዎቻቸውን የማቅረብ ዕድል አገኙ፤ ጊዜው 1969 ዓ.ም ነበር።

በርካቶች ተጋብዘውበት በነበረው በዚህ መድረክ እውቅናን ማትረፍ ቻሉ።

ከዚያም ብዙም ሳይቆይ በዓመቱ 1970 ዓ.ም የላሊበላ የባህል ቡድን በደሴ ከተማ ተቋቋመ። ለሙያው ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች ተሰባስበውና ቀለመወርቅ ደበበ የተባሉ አሰልጣኝ ከአዲስ አበባ ተመድበውላቸው መሥራት ጀመሩ።

ሙያተኞቹ ቀድመው ሰው ልብ ውስጥ ነበሩና የኪነት ቡድኑ ዝና ለማትረፍ ጊዜ አልፈጀበትም።

ቡድኑ እንዲበተን እስከተደረገበት 1983 ዓ.ም ድረስም የተለያዩ የሙዚቃ ሥራዎችን ሲያበረክት ቆይቷል።

ከዚያ በኋላ በተለያየ ጊዜ ቡድኑን ለማሰባሰብ ጥረት ሲደረግ ቆይቶ በ2005 ዓ.ም በደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ፣ በወሎ ዩኒቨርሲቲ እና በሌሎች አጋር ተቋማት አማካኝነት እንደገና ተደራጀ።

አሁን ላይ በወሎ ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኘው የኪነት ቡድኑ ለተተኪዎች ሥልጠና በመስጠት፣ ባህልና ልምዳቸውን በማካፈል የበኩሉን እያበረከተ ይገኛል።

የወሎ ላሊበላ ኪነት የራሱን ገቢ ያገኝ ዘንድም 'ላኮመልዛ ኢንተርፕራይዝ' ወደሚል መሸጋገሩን የዞኑ የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ሶለሂማን ገልጸዋል።