በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በአንድ ሳምንት ውስጥ 42 ሰዎች በኮቪድ ተያዙ

የፕሪሚየር ሊግ ኳስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በእንግሊዝ በፕሪሚየር ሊግ በአንድ ሳምንት ውስጥ 42 ሰዎች በኮቪድ መያዛቸው መረጋገጡን ተከትሎ የሊጉ መረሃ ግብር መቀየር ግድ እንዲሆን አድርጓል።

ባለፈው ሳምንት አርባ ሁለት የፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾች እና ሠራተኞች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተረጋገጠ። ይህም በሊጉ በሰባት ቀናት ጊዜ ውስጥ የተመዘገበው ከፍተኛው ቁጥር ነው።

ይህም በጥር ወር 40 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ከተመዘገበበት ወዲህ ከፍተኛው ቁጥር ነው።

ብራይተን፣ ቶተንሃም፣ ሌስተር፣ ማንችስተር ዩናይትድ፣ አስቶንቪላ እና ኖርዊች በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን ያረጋገጡ ክለቦች ሲሆኑ ዩናይትድ ከብሬንትፎርድ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በዚሁ ምክንያት ተራዝሟል።

የእሑዱ የብራይተን እና የቶተንሃም ጨዋታም በኮቪድ-19 በስፐርስ ቡድን መከሰቱን ተከትሎ መራዘሙ ይታወሳል።

በእንግሊዝ አዲስ የኮሮናቫይረስ ክልከላዎች መተግበርን ተከትሎ ሐሙስ ዕለት የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች አካላዊ ርቀትን እና ጭንብል ማድረግን ጨምሮ ወደ ጥንቃቄ እርምጃዎች እንዲመለሱ ተነግሯቸዋል።

ሰኞ ዕለት ሊጉ በመግለጫ እንዳስታወቀው በተጫዋቾች እና በክለብ ሠራተኞች የሚደረገው ምርመራ ይጨምራል።

መግለጫው አክሎም "ለወደፊት ለሚደረጉ የጥንቃቄ ለውጦች ምላሽ እየሰጠን ከመንግሥት፣ ከአካባቢ ባለስልጣናት እና ከድጋፍ ሰጪ አካላት ጋር በቅርበት መሥራታችንን እንቀጥላለን" ይላል።

ከረቡዕ ጀምሮ ደጋፊዎች በእንግሊዝ ከ10,000 በላይ ሰዎች በሚሰባሰቡባቸው የስፖርት ዝግጅቶች ላይ ለመሳተፍ ሙሉ ክትባት የወሰዱ ወይም ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ማሳየት አለባቸው። ይህ ደግሞ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችንም ይጨምራል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በየትኞቹ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ተገኘ?

የቶተንሃም የዩሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ጨዋታ ከሬኔስ ጋር ሐሙስ ሊያደርገው የነበረው ጨዋታ ተሰርዟል። ምክንያቱ ደግሞ ክለቡ ከብራይተን ጋር የነበረው ጨዋታ ለሌላ ጊዜ እንዲራዘም ባደረገው ወረርሽኝ ምክንያት ነው።

ሐሙስ ዕለትም በርካታ የሌስተር ተጫዋቾች ቫይረሱ እንደለባቸው በምርመራ በመረጋገጡ ከናፖሊ ጋር በዩሮፓ ሊግ የምድብ ጨዋታቸውን ለማድረግ ወደ ጣሊያን አልተጓዙም።

የአስቶንቪላው አሰልጣኝ ስቴቨን ዤራርድ "ሁለት ሠራተኞች እና ሁለት ተጫዋቾች" ቫይረሱ እንደተገኘባቸው አረጋግጦ ነገር ግን "አብዛኞቹ" ውጤታቸው ነጻ መሆኑን ተናግሯል።

ማክሰኞ ከኖርዊች ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ እንደሚካሄድ ገልጿል። የካናሪሱ አለቃ ዲን ስሚዝ በበኩሉ ከተጫዋቾቹ አንዱ የተገለለ ቢሆንም የተቀረው የቡድን አባላቱ እሑድ በተደረገ ምርመራ ነጻ ሆነዋል።

በብራይተን አሰልጣኝ ግርሃም ፖተር በበኩሉ "ሦስት ወይም አራት" ተጫዋቾች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

በፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ ስለሚገኙ ደጋፊዎች ህጎቹ ምን ይላሉ?

መንግሥት የኦሚክሮን ዝርያን መስፋፋትን ለመከላከል ረቡዕ ዕለት ባስተዋወቀው ሁለተኛ ዕቅድ በእንግሊዝ ከ10,000 በላይ ሰዎች በሚሰባሰቡባቸው የስፖርት ዝግጅቶች ላይ ለመገኘት ደጋፊዎቸ ሁለቴ ስለመከተባቸው ማረጋገጫ ወይም ከቫይረሱ ነጻ ስለመሆናቸው መረጋገጫ ማሳየት ይኖርባቸዋል።

ረቡዕ ምሽት ብራይተን በፕሪሚየር ሊጉ ከዎልቭስ ጋር ይጫወታል። የሲጉልሱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፖል ባርበር ደጋፊዎቻቸው አዳዲስ መመሪያዎች እስከተከተሉ ድረስ ጨዋታዎችን በሚከታተሉ ደጋፊዎች ቁጥር ላይ እገዳዎች አይመለሱም የሚል ተስፋ አለኝ ብለዋል።