ሱዳን ከኢትዮጵያ የሚያዋስናት ድንበር ላይ ተጨማሪ ወታደሮችን አሰፈረች

የሱዳን ሠራዊት አባላት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በምትወዛገብበት ድንበር ላይ ተጨማሪ ወታደሮችን ማስፈሯን ጦሯ አስታወቀች።

ምንም እንኳን ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ውጥረት እንደቀጠለ ቢሆንም ቀጠናው ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ስር እንደሆነም የጦሩ አመራሮች አስረድተዋል።

ጦሩ ለዜጎቹ ባስተላለፈው መልዕክት "የሰላም እንቅልፍ ተኙ" ብሏል።

ሱዳን ኅዳር 22/2014 ዓ.ም ባስታወቀችው መሰረት በአወዛጋቢው አል ፋሽቃ አካባቢ የሰፈሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ጋር የተኩስ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ አካባቢውን መቆጣጠሯንና ወታደሮቹንም ከጥቅም ውጭ ማድረጓን አስታውቃለች።

ድል መቀናጀቷን ከማወጇ ከአራት ቀናት በፊት አወዛጋቢ በሆነው ብርካት ኑራይን በተባለ አካባቢ ከኢትዮጵያ ጦር ጋር በተፈጠረ ግጭት 21 የሱዳን ወታደሮች ሲገደሉ 30 ሰዎች ቆስለዋል የሚል ዘገባም ወጥቶ ነበር።

ሱዳን በኢትዮጵያ ሠራዊት ጥቃት እንደተፈጸመባትና ወታደሮች እንደተገደሉባት ባሳወቀችበት ወቅት ኢትዮጵያ ግን ክሱን ማስተባበሏ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም እና የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር የአገሪቱ ሠራዊት ጥቃት አለመፈጸሙን ነገር ግን በድንበር በኩል ሰርገው ለመግባት በሞከሩ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል ያገረሸው ውትረት አሁንም የመባባበስ ሁኔታ እያሳየ ሲሆን የሱዳኑ ወታደራዊ ገዢ ሌተናል ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሐን አገራቸው ለኢትዮጵያ "ቅንጣት መሬት" እንደማይሰጡ ተናግረዋል።

ጥቅምት 24/ 2013 ዓ.ም ትግራይ ውስጥ ጦርነት ሲቀሰቀስ ኢትዮጵያ በአርሶ አደሮቿ ይዞታ ስር ከነበሩት፣ ሱዳን ይገባኛል ከምትለውና በሠራዊቷ ከሚጠበቀው አወዛጋቢ የድንበር አካባቢ ወታደሮቿን ማስወጣቷን ተከትሎ ነበር ሱዳን ቦታውን በኃይል የተቆጣጠረችው።

በዚህም በርካታ አርሶ አደሮችና ሠራተኞች ለመፈናቀል ከመዳረጋቸው በተጨማሪ የእርሻ ስፍራዎች ላይ ውድመት፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት ላይ ደግሞ ዝርፊያና ውድመት መፈጸሙን ቢቢሲ በወቅቱ ዘግቦ ነበር።

ኢትዮጵያ የሱዳን ሠራዊት ከያዛችው ቦታዎች በመውጣት ለዓመታት ሲካሄድ ወደነበረው ውይይት እንድትመለስና ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ብትጠይቅም፣ ከሱዳን በኩል ምላሽ ሳያገኝ እስካሁን ቆይቷል።

የአልፋአካባቢ

ሱዳንና ኢትዮጵያ በይገባኛል ከሚወዛገቡበት አካባቢ በተጨማሪ ረዥም የጋራ ድንበር ይጋራሉ። ሁለቱም አገሮች አወዛጋቢውንና ለም ነው የሚባለውን አልፋሽቃ አካባቢ በእጅጉ ይፈልጉታል።

ይህ በሁለቱ አገሮች ዓይን ውስጥ ያለው አካባቢ የአልፋሽቃ ማዕዘን ወይም የአልፋሽቃ ጥግ ተብሎ ይጠራል።

በዚህ ድንበር በሁለቱም ወገን የሚገኙ ገበሬዎች ለም መሬቱ ላይ ያማትራሉ። አልፋሽቃ ማዕዘን ከሱዳን በስተምሥራቅ ከኢትዮጵያ ደግሞ በስተምዕራብ የሚገኝ ለእርሻ አመቺ በተለይ ደግሞ ለቅባት እህሎች ምርት የሚውል ለም መሬት የያዘ ቦታ ነው።

አልፋሽቃ መሬት 250 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍንና 600 ሺህ ኤክር ለም መሬትን የሚሸፍን ነው። ለለምነቱ ምክንያት የሆኑት እንደ አትባራ፣ ሰቲት እና ባስላም ወንዞች በቅርብ ይገኛሉ።

የሱዳን ባለሥልጣናት አልፋሽቃ የሱዳን ግዛት ነው ይላሉ። ታዲያ በኢትዮጵያውያን እጅ ለምን ቆየ ሲባሉ፣ "የሱዳን መንግሥት ከአገሪቱ ጋር ባለው የትብብርና የመግባባት ስምምነት መንፈስ ነው የኢትዮጵያ ገበሬዎች ቦታውን እያለሙት የነበረው" ይላሉ።

በኢትዮጵያ በኩልም ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ለዘመናት በቦታው ሰፍረው እያረሱ የኖሩበት የአገሪቱ ግዛት መሆኑን በመግለጽ የሱዳንን እርምጃ "ወረራ" ሲሉ ይገልጹታል።

ሁለቱ መንግሥታት ከዚህ ቀደም ይህንን አወዛጋቢ ድንበር ለመለየትና ለማካለል፣ የጋራ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር እና የአካባቢውን ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።

ቀደም ሲል የነበረው አስተዳደር የኢትዮጵያ መንግሥት የአገሪቱን ሉአላዊ መሬት ለሱዳን ቆርሶ ለመስጠት ተስማምቷል በሚል ተደጋጋሚ ወቀሳ ሲቀርብበት ቢቆይም ይዞታው በኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ስር ቆይቷል።

እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2014 የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የወቅቱ ሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸውን ድንበሩ መሬት ላይ የሚመላከትበትን የመጨረሻ ውሳኔ እንዲያሳውቁ መመሪያ አስተላልፈው ነበር።

ሆኖም ግን አወዛጋቢውን ድንበር ለዓመታት መሬት ላይ የማመላከቱ ሥራ ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቶ፣ ሁለቱም መሪዎች ከስልጣን ለቀው ሱዳን አካባቢውን በኃይል ተቆጣጥራዋለች።