በባሏ እጇ ለተቆረጠባት ሴት የሩሲያ መንግሥት ካሳ እንዲከፍል ተፈረደበት

ማርግሬታ ግራቼቫ ሆስፒታል ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Margarita Gracheva

የምስሉ መግለጫ,

ማርግሬታ ግራቼቫ ሆስፒታል ውስጥ

ሩሲያ በባሏ እጇ ለተቆረጠባት ሴት ከ370 ሺህ ዩሮ በላይ ካሳ እንድትከፈል በአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት ተፈደባት።

ፍርድ ቤቱ ሩሲያ በሴቶች ላይ በቤት ውስጥ የሚፈጸመውን ጥቃት ለመከላከል ሳትችል ቀርታለች በሚል ነው ውሳኔውን ያሳለፈው።

እጇ ከተቆረጠው ሴት በተጨማሪ በአሰቃቂ ሁኔታ ጥቃት ለተፈጸመባቸው ሌሎች ሴቶችም ካሳ እንዲከፈል ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

ከእነዚህ ሴቶች መካከል ከአራት ዓመት በፊት በባሏ ታፍና ወደ ጫካ ከተወሰደች በኋላ በመጥረቢያ እጇቿ የተቆረጠባልት ማርጋሪታ ግራቼቫ የተባለች ሴት አንዷ ናት።

ግለሰቧ የባለቤቷን ነውጠኛ ባህሪይ በተመለከተ ከጥቃቱ ቀደም ብላ ለፖሊስ አመልክታ የነበረ ቢሆንም አቤቱታዋ ችላ ተብሎ ለአሰቃቂው ጥቃት ተደርጋለች።

ከጥቃቱ በኋላ የተቆረጠው የግራ እጇ ከጫካ ውስጥ ተገኝቶ በቀዶ ህክምና ወደ ቦታው እንዲመለስ ተደርጓል። በጥቃቱ የተቆጡ ሰዎች በሰበሰቡት መዋጮ ደግሞ ሰው ሰራሽ የቀኝ እጅ ተገጥሞላታል።

ጥቃቱን የፈጸመባት የቀድሞ ባሏ በፈጸመው ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የ14 ዓመታት አስር ተፈርዶበታል።

ፍርድ ቤቱ ጨምሮም ሩሲያ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ተመሳሳይ በደሎችን ለማስቆም የሚያስችል አስቸኳይ ለውጥ እንድታደርግ አዟል።

በሩሲያ በሴቶች ላይ በቤት ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶች "በከፍተኛ ሁኔታ" እየተከሰቱ መሆናቸውን ፍርድ ቤቱ ጠቅሶ፣ በዚህም ሩሲያ የአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ስምምነትን ሁለት አንቀጾችን ጥሳለች ብሏል።

ፍርድ ቤቱ የግራቼቫን ጉዳይ በማንሳት ባለሥልጣናትና ሕግ አስፈጻሚዎች በሴቶች ላይ በቤት ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶች አካላዊ ጉዳት አስኪያስከትል ድረስ ለመከላከል አልቻሉም ብሏል።

የጥቃት ሰለባ የሆኑት ሴቶች ካሳ እንዲከፈላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ ሩሲያ ቀደም ሲል ውድቅ አድርጋው ነበር።

የአውሮፓ ሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የሩሲያ ምክትል ጠፍትሕ ሚኒስትር ሚኻይል ጋልፔሪን እንደተናገሩት፣ በግለሰቦች በቤት ውስጥ ለሚፈጸም ጥቃት መንግሥት ተጠያቂ ሊሆን አይገባም ብለዋል።

ከአራት ዓመት በፊት ፕሬዝዳንት ፑቲን በቤት ውስጥ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች የሚወሰን ቅጣትን የሚያላላ ሕግ ፈርመዋል። በዚህም የመጀመሪያ ጥቃት ሆኖ ተጎጂዋን ለሆስፒታል የማያበቃት ከሆነ የወንጀል ጥፋት እንዳይሆንና ቅጣቶችም እንዲቀነሱ አድርጓል።