የቤልጂየም ጌነት ዩኒቨርስቲ፡ ጦርነቱ ባስከተላቸው ቀውሶች በትግራይ ምን ያህል ሰዎች ሞተው ይሆን?

ሐዘናቸውን የሚገልጹ እናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቅርቡ በቤልጂየም የጌነት ዩኒቨርስቲ በትግራይ ክልል በጦርነቱ፣ በረሃብና መድኃኒት እጦት እስካሁን ድረስ ከ300 ሺህ እስከ 500 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ሞተዋል ሲል የጥናት ውጤቱን ይፋ አድርጓል።

ጥናቱን በበላይነት የመሩት ፕሮፌሰር ጃን ኔይሰን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጦርነቱ በትግራይ ክልል ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሲከታተሉ እንደነበር ገልፀዋል።

ፕሮፌሰር ጃን ከዚህ በፊት በትግራይ እና በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች በአፈር መሸርሸር ላይ የተለያዩ ጥናቶችን ሲሰሩ እንደነበር አስታውሰው ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በመቀለ እንዲሁም የተለያዩ የትግራይ የገጠር ቀበሌዎች ያሏቸውን የመረጃ ምንጮች ተጠቅመው የደረሱ ሞቶችን መሰነዳቸውን ይናገራሉ።

የፌደራል መንግሥቱ ከትግራይ ክልል የህወሓት አማፂያን ጋር ወደ ጦርነት የገባው ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ሲሆን ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በጦርነቱ ምክንያት ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ የወጣ ይፋዊ መረጃ የለም።

ፕሮፌሰር ጃን ይህንን ክፍተት በማስተዋል "ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከሌሎች የሥራ ባልደረቦች ጋር በመሆን ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ የተፈጸሙትን ግድያዎች መረጃ ለመከታተልና ለመሰብሰብ ወሰንን" ይላሉ።

እንደ ፕሮፌሰር ጃን ገለጻ ከሆነ ከደረሱ የጅምላ ጭፍጨፋዎች ውስጥ ወደ 10 ሺህ የሚሆኑ ሟቾችና ተጎጂዎችን ማንነት መሰነድ ችለዋል።

"አንዳንድ ጊዜ የተገደሉበት ጊዜና ቦታ ለማጣራት ከባድ ነበር፤ አንዳንድ ሰዎች በኢትዮጵያ አቆጣጠር ነው የሚነግሩህ፤ ይሄ ሁሉ በተወሰነ ደረጃ አስቸጋሪነት ነበረው። ሆኖም ሁሉንም መረጃ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለማመሳከርና፤ ለመናበብ ሞክረናል።"

በዚህ መንገድ በክልሉ በጅምላ ጭፍጨፋ የተገደሉት 50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ሰዎች እንደሚደርሱ ይናገራሉ።

አስካሁን በቤልጂየም ዩንቨርስቲ ፕሮፌሰር ከወጣው ከዚህ አሃዝ ውጪ ከየትኛውም ወገን ከጦርነቱ ጋር ተያይዘው በተከሰቱ ችግሮች ምክንያት በትግራይ ክልል ህይወታቸው ያለፈ ሰዎችን ቁጥር የሚያመለክት መረጃ አልወጣም።

በተጨማሪም ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ከሌሎች አካላት ይህንን አሃዝ በተመለከተ የተባለ ነገር የለም።

ረሃብ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት

ፕሮፌሰር ጃን በጥናታቸው በረሃብ የሞቱትን ጨምረው ማካተታቸውን በመግለጽ፤ ለዚህም እንደመነሻ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከወራት በፊት አስከ 400 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች እንዲሁም ዩኤስኤአይዲ እስከ 900 ሺህ ሰዎች በረሃብ አደጋ ውስጥ ስለመሆናቸው ካስቀመጡት በመሳት ቁጥሩን ማጠናቀራቸውን ገልጸዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግሥታት በትግራይ ክልል ያሉ 6 ሚሊዮን ሰዎችን ይፋዊ ባልሆነ እቀባ ሥር አድርገዋል ሲሉ ባለፈው ሳምንት ተናግረው ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ከሆነ በክልሉ ከ5.2 ሚልዮን በላይ ሕዝብ አስቸኳይ እርዳታ የሚጠባበቅ ሲሆን ግማሽ ሚሊዮን ያህሉ የክልሉ ሕዝብ ደግሞ ለከፍተኛ ረሃብ ተጋልጧል።

የትግራይ ቴሌቪዝን የክልሉ ማኅበራዊ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ደባልቀውን ጠቅሶ ባሰራጨው ዘገባ "በቅርብ ጊዜ እርዳታ ካልገባ ከግማሽ በላይ የትግራይ ሕዝብ ያልቃል" ብሎ ነበር።

እኚሁ ኃላፊ "እቀባው እየበረታ በመሄዱ በመጥፋት አፋፍ ላይ እንገኛለን፤ እቀባው እስከ ሚያዚያ ድረስ ከቀጠለ ግማሽ የትግራይ ሕዝብ ያልቃል፤ ብዙዎች በመድኃኒት እጥረት እየሞቱ ነው።

ለቤተሰቦቻቸው መሰረታዊ አቅርቦት ማቅረብ ባለመቻላቸው ደግሞ "በርካቶች ራሳቸውን እያጠፉ እንዳሉ ሪፖርቶች እየደረሱን ነው" ሲሉ ተናግረው ነበር።

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የሚወጡ ሪፖርቶች እንዳመለከቱት ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በትግራይ ክልል ያለውን ረሃብና ችግር በመሸሽ ወደ አማራ ክልል እገቡ መሆናቸው ይነገራል።

የፎቶው ባለመብት, AFP

እንዴት እዚህ አሃዝ ላይ ተደረሰ?

ፕሮፌሰር ጃክ ስለ ጥናታቸው ውጤት ለቢቢሲ ባስረዱበት ወቅት እዚህ ቁጥር ላይ ለመድረስ ከጦርነቱ በፊት ባሉት ዓመታት የነበረውን የሞት መጠንን መመልከታቸውን ያስረዳሉ።

ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ መረጃዎችን ከዩኤስአይድ መውሰዳቸውን እና መጠቀማቸውን ጨምረው ገልፀው "ከ400 ሺህ እስከ 900 ሺህ ሰዎች በረሃብ ሊሞቱ እንደሚችሉ ነው ያስቀመጠው" ይላሉ።

ይህ የዩኤስ አይዲ መረጃ በየቀኑ "ከ10 ሺህ ሰዎች ውስጥ ሁለት ሰዎች" እንደሚሞቱ እንደሚያሳይ በመግለጽ ይህ ትልቅ ቁጥር እንደሚሰጥ ያስረዳሉ።

ከዚህም በተጨማሪ በመድኃኒት ዕጦት የሚሞቱ መኖራቸውን ፕሮፌሰር ጃክ ያስረዳሉ።

"በዓይደር ሆስፒታል መጥተው መድኃኒት አጥተው የሞቱ ሰዎች በተመለከተ መረጃ አለን። ይሄ ትንሽ ፍንጭ ነው የሚሰጥህ። ከባሕር በጭልፋ ነው።"

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ በትግራይ ክልል የነበሩ የሕክምና ተቋማት መውደማቸውን ገልጾ ከውደመት የተረፉትም በመድኃኒትና የሕክምና መሳሪያዎች እጥረት ሊሰሩ ወደማይችሉበት ደረጃ መወርዳቸውን ማስታወቁ ይታወሳል።

"የሕክምና አገልግሎት አቅራቢዎች መሠረታዊ ግብዓቶችን እያገኙ አይደለም፤ እንዲሁም በአንዳንድ መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል" ብሏል ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ (አይሲአርሲ) ጥር 09/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ።

ቀይ መስቀል የመድኃኒት እና ሕክምና መስጫ መሳሪዎች እጥረት ከጤና መሠረተ ልማት ውድመቶች ጋር ተደማምሮ የጤና አገልግሎት አቅርቦትን እጅግ አስቸጋሪ አድርጎታል ይላል።

ፕሮፌሰር ጃክ በበኩላቸው በዚህ ጥናት በዓይደር ሆስፒታል የሚሰሩ ሰዎችን ማናገራቸውን እና በመድኃኒት ዕጦት ስንት ሰው እንደሞተ መረጃ ማግኘታቸውን ገልፀዋል።

"ለምሳሌ በውሻ ተነክሶ የሞተ ተማሪ ነበር። ክትባት ማግኘት አልቻሉም። ሌላ ጊዜ ቢሆን ሊድን የሚችል የነበረ ነው። መሞት አልነበረበትም።"

እየጨመረ ያለ የሞት መጠን

በመድኃኒት እጦት ስንት ሰዎች እንደሞቱ እንዴት እንዳሰሉም ሲያስረዱ "በፊት ጦርነት ባልነበረበት ጊዜ ከሚሞቱት ጋር ማነጻጸር ነበረብን፤ [የሞት መጠን የመዘገቡበት ግራፍ ይጠቅሳሉ] ይህ ግራፍ የሞት መጠኑ እንዴት ወደ ላይ እንዳሻቀበ የሚያሳይ ነው።"

"አንዳንድ ግኝቶችን ለመጥቀስ፡ በ1980 (እኤአ) ዘመናዊ የጤና ሥርዓት ባልነበረበት ጊዜ ከ1000 ሰዎች 20 ሰዎች ይሞቱ ነበር። ይሄ ጦርነት እስከ ተጀመረበት ጊዜ የሞት መጠኑ ወደ 6 ሰው ከ1000 ማውረድ ተችሎ እንደ ነበር መረጃዎች ያሳያሉ" ብለዋል።

አሁን ግን የሞት መጠን መልሶ ጨምሯል ያሉት ፕሮፌሰሩ አብዛኞቹ የሕክምና ተቋማት መውደማቸውን፣ ያሉትም ያለ ሕክምና መሳሪያ እና ባለሙያ መቅረታቸውን በመጥቀስ "ዘመናዊ የህክምና ሥርዓት ከመስፋፋቱ በፊት ወደ ነበረበት ዘመን ተመልሰናል ማለት ነው" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP

አክለውም "የእኛ ግምት የሞት መጠኑ ከ1000 ሰው 20 ወደሚሞትበት ተመልሷል የሚል ነው። . . . በዚያ ላይ ምንም አይነት የመድኃኒት አቅርቦት ወዳልነበረበት ጊዜ ተመለስን ብንል ደግሞ የሞት መጠኑ 32 ሰው ከ1000 ይሆናል። ይህ መረጃ ሜዲካል ዶክተሮችም የተስማሙበት አሃዝ ነው" ይላሉ።

በአሁኑ ወቅት ወደ ትግራይ ክልል የሚገባው የሰብዓዊ እርዳታ አነስተኛ በመሆኑ እና በቀጠለው ጦርነት ምክንያት ስለሚደናቀፍ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ እንደተፈጠረ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ይገልጻሉ።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ትግራይ ውስጥ ብቻ 4.6 ሚሊዮን ሰዎች፣ ማለትም ከአምስት ሰዎች መካከል አራቱ የምግብ እህል እርዳታ ጠባቂዎች መሆናቸውን ይናገራል።

በተጨማሪም የፌደራል መንግሥት እና የህወሓት አማፂያን ወደ ክልሉ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ የሚደርስበትን መንገድ እንዲያመቻቹ ሲጠይቅ ቆይተዋል።

ወደ ክልሉ ሰብዓዊ እርዳታ ላለመግባቱ ግን ህወሓት አመራሮች እና የፌደራል መንግሥቱ እርስ በእርስ ይወነጃጀላሉ።

'የባሰ ሊከሰት ይችላል'

ፕሮፌሰር ጃን ወደ ትግራይ በፍጥነት እርዳታ የማይደርስ እና ሁኔታው በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ የከፋ ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ይገልጻሉ።

"የባሰ ሊሆን የሚችል ነው ሚመስለኝ የሞት መጠን በእጅጉ ይጨምራል። በእርግጥ በቁጥር ይሄን ያህል ሰው ሊሞት ይችላል ብዬ በአሀዝ ለማስቀመጥ ይከብደኛል" ብለዋል።

"እስካሁን ባለው ሁኔታ በእኛ ግምት ከ300 ሺ እስከ 500 ሺሕ ሰዎች ህይወታቸውን እንዳለፈ ነው። ስለዚህ ሁኔታው የማይሻሻል ከሆን፣ የሞት መጠኑ በብዙ እጥፍ [exponencial] ስለሚጨምር በሚልዮን የሚቆጠር ሕዝብ ሊያልቅ ይችላል" ይላሉ።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በጥር ወር መጨረሻ ላይ ይፋ ባደረገው መረጃ 40 በመቶ የሚሆነው የትግራይ ሕዝብ "ለከባድ የምግብ እትረት" ተጋልጧል ብሏል።

ይህ ሪፖርት 83 በመቶ የሚሆኑት የክልሉ ነዋሪዎች ምግብ እንደጨረሰና ልመና ላይ ተሰማርተው በቀን አንድ ጊዜ ብቻ እየተመገቡ እንዳሉ ያመለክታል።

በተጨማሪም አሁን በአፋር ክልል በኩል በቀጠው ግጭት የተነሳ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ የሚያልፍበት ብቸኛው የሰመራ-አብዓላ መንገድ እንደዘጋው በተደጋጋሚ ተገልጿል።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በክልሉ ውስጥ ያላቸው የእርዳታ አቅርቦት እና ነዳጅ ክምችት እንደተሟጠጠ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በመጓጓዣ እና ነዳጅ እጥረት ምክንያት እርዳታቸውን ለመቀነስ እንደተገደዱ አስታውቀዋል።

እስከ መጋቢት 08/2022 (እኤአ) ባለው ጊዜ ውስጥም በአጠቃላይ 600 ሊትር ነዳጅ ብቻ እንደቀራቸው ገልፀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓለም ምግብ ድርጅት ለቢቢሲ በአሁኑ ወቅት በአፋር አብዓላ መስመር ወደ ትግራይ እየተጓጓዘ ያለ የሰብዓዊ እርዳታ አለመኖሩን ገልጾ፣ በቅርቡ ግን የፌደራል መንግሥቱ እና የአፋር ክልል ባለሥልጣናት የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዲደርስ መፍቀዳቸው አረጋግጧል።