የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ማልያዎች ለምን ውድ ሆኑ?

የማንቸስተር ሲቲ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች

እየጨመረ የመጣው የማልያዎች ዋጋ ከፍተኛ መሆን እና በተለይ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ትልልቅ ክለቦች ማልያቸውን መቀያየራቸው አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል። የእንግሊዙ ሊድስ ዩናይትድ በ1973 የክለቡን መለያ በ7 ዶላር መሸጥ ከጀመረ ወዲህ የማሊያዎች ዋጋ እጅጉን የጨመረ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት ይህ ዋጋ ከ10 እጥፍ በላይ ጨምሯል።

ከ2011/2012 ውድድር ዘመን ጀምሮ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ማልያዎች ዋጋ በ18.5 በመቶ ጨምሯል። በቅርቡ በተደረገ ጥናት መሰረት በዚህ ዓመት የአንድ ትልቅ ሰው ማልያ 68 ዶላር ያወጣል።

በጣም ውድ የሆኑት ማልያዎች የትኞቹ ናቸው?

የማንቸስተር ሲቲ፤ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ቶተንሃም ሆትስፐር መለያ ልብሶች ከ80 እስከ 88 ዶላር ይሸጣሉ።

አሁን ባለው የእግር ኳስ ባህል ደግሞ የማልያዎች መሸጫ ዋጋ ብቻ አይደለም እየጨመረ ያለው፤ የማልያዎች ቁጥርም እንጂ። ለቡድኖች ሶስተኛ ተቀያሪ ማልያ ማዘጋጀት ልምድ እየሆነ መጥቷል።

የ1968ቱን የውድድር ዘመን ለማስታወስ ተብሎ 145 ሚሊየን ዶላር ወጪ ተደርጎበት የተሰራው የማንቸስተር ዩናይትድ ሰማያዊ መለያ በደጋፊዎች ስላልተወደደ ለኪሳራ ተዳርጎ ነበር። ታድያ እነዚህ መለያዎች ውድ ናቸው ተብሎ ቢታሰብም፤ በሌሎች የአውሮፓ ሃገራት የሚገኙ ደጋፊዎች ግን ከዚህም በላይ ነው የሚከፍሉት።

በጣልያን ደጋፊዎች በአማካይ እስከ 90 ዶላር ድረስ የሚከፍሉ ሲሆን፤ በፈረንሳይ እና ጀርመን ያሉ ደጋፊዎች ደግሞ ከ91 እስከ 95 ዶላር ድረስ ይከፍላሉ።

ዋጋዎች ይህን ያህል ለምን ተጋነኑ? ብለን ስንጠይቅ፤ በዋነኛነት የሚጠቀሰው ምክንያት በማሊያዎች ምርት ወቅት ስፖንሰር የሚያደርጉት ድርጅቶች ወጪያቸውን ለመሸፈን ሲሉ በማሊያዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ ያደርጋሉ።

የእግር ኳስ ቡድኖች ሶስት ዋነኛ ገቢ ምንጮች አሏቸው። ከእያንዳንዱ ጨዋታ የሚገኝ ገቢ፤ ከመገናኛ ብዙሃን የሚገኝ ገቢ እና እንደ ማልያ ካሉ የተለያዩ ምርቶች ሽያጭ የሚገኝ ገቢ።

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሚጫወቱት 20 የእግር ኳስ ቡድኖች ከባለፈው ዓመት 73.65 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ በማሳየት በ2017/2018 ስፖንሰር ከሚያደርጉ ድርጅቶች ጋር ለቲሸርት ብቻ የ377.36 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ፈጽመዋል።

ይሄ ሁሉ ገንዘብ ግን የት ነው የሚሄደው?

ምንም እንኳን ደጋፊዎች የማልያዎችን ዋጋ ቀንሱልን ብለው ክለቦቹን ቢጠይቁም፤ እውነታው ግን ከፍተኛ የሚባለው ትርፍ የሚገባው እንደ 'ናይክ'፤ 'አዲዳስ' እና 'ፑማ ላሉ ጥቂት አምራች ድርጅቶች ነው።

'ናይክ' ብቻውን በሶስት ወራት ያገኘው ገቢ ሁሉም የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች በቀጣዩ ዓመት ከሚያስገቡት ገቢ ይበልጣል።

በአጠቃላይ 80.35 ዶላር ከሚያወጣ መለያ 5.8 በመቶ የሚሆነው ወጪ ለጨርቅ፤ ለስፌትና ለማጓጓዣ ነው የሚውለው። በዚህ መሰረት 11.5 በመቶ የሚሆነው ትርፍ ለአምራቹ ሲሆን፤ 3.6 በመቶው ለእግር ኳስ ክለቦቹ ነው። አከፋፋዮች ደግሞ ከሽያጭ ከሚገኘው ገቢ 22 በመቶውን ይወስዳሉ፤ ቀሪው ለግብር፤ ለማከፋፈያ ወጪዎችና ማስታወቂያ ላይ ይውላል።