ፈረንሳይና ክሮሺያ ለዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ለመድረስ ያለፉበት መንገድ

የፍጻሜው ጨዋታ የሚካሄድበት ሊዥኒኪያ ስታዲየም

በመጪው እሁድ በሚካሄደው ለዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ለሦስተኛ ጊዜ የደረሰችው ፈረንሳይና በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዋንጫ የምትጫወተው ክሮሺያ ይገናኛሉ። እነዚህ ቡድኖች በሉዥኒኪ ስታዲየም ለሚደረገው የፍጻሜው ጨዋታ ለመድረስ ያደረጉት ጉዞ ምን ይመስል ነበር?

ፈረንሳይ

ከአውስትራሊያ ጋር ያደረጉት የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ እጅግ ፈታኝ የሚባል ነበር። በሩሲያው የዓለም ዋንጫ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በቪዲዮ የታገዘ የፍጹም ቅጣት ምት ያገኙት ፈረንሳዮች፤ የዓለም ዋንጫውን የመጀመሪያ ግባቸውን ያስቆጠሩት በዚሁ ፍጹም ቅጣት ምት ነበር። ጨዋታው በፈረንሳይ 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የምድቡ ሁለተኛ ጨዋታቸው ደግሞ ከፔሩ ጋር ነበር። ብዙዎችን እያስደመመ የሚገኘው የ19 ዓመቱ ኪልያን ምባፔ ባስቆጠራት የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ግቡ ጨዋታውን አሸንፈው ወጥተዋል።

ስለዓለም ዋንጫ የሚያሰረዱ ሰባት መረጃዎች

ቢጫና ቀይ ካርዶች እንዴት ወደ እግር ኳስ ሜዳ መጡ?

የእግር ኳስ ማልያዎች ለምን ውድ ሆኑ?

ከሁለተኛው ጨዋታ በኋላ ከምድቡ ማለፋቸውን ያረጋገጡት ፈረንሳዮች የመጨረሻ የምድብ ተጋጣሚያቸው ዴንማርክ ነበረች። ይህ ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ፈረንሳይ ሦስት ግብ አስቆጥራ አንድ ግብ ብቻ አስተናግዳ ከምድቡ አንደኛ ሆና መጨረስ ችላለች።

ከዚህ በመቀጠል ፈረንሳይ 16ቱን ሃገራት ከተቀላቀለች በኋላ የተገናኘችው 5 ጊዜ የባለንዶር ሽልማትን ያነሳው ሊዮኔል ሜሲን ካካተተው አርጀንቲና ጋር ነበር። በዚህኛው ዓለም ዋንጫ ካየናቸው ድንቅ ጨዋታዎች አንዱ የነበረው ይህ ፍልሚያ በፈረንሳይ 4 ለ 3 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የ19 ዓመቱ ምባፔ ሁለት ግቦች ባስቆረበት በዚህ ጨዋታ፤ ሁለት ለአንድ ከመመራት ተነስተው ነው ጨዋታውን ማሸነፍ የቻሉት።

Image copyright Getty Images

ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት ያላስተናገዱት ፈረንሳዮች ወጣት ተጫዋቾቻቸውን ይዘው የደቡብ አሜሪካዋን ኡራጓይ በሩብ ፍጻሜው ለመግጠም ተዘጋጁ።

ብዙዎች ፈረንሳዮች እስካሁን አልተፈተኑም፤ አሁን ግን ከባድ ፈተና ከኡራጓይ ይገጥማቸዋል ብለው ቢያስቡም፤ ጨዋታውን ሁለት ለባዶ በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ማለፍ ችለዋል።

ለፍጻሜው ጨዋታ መድረሳቸውን የሚያረጋግጡት ግን በውድድሩ ብዙ ግቦችን ያስቆጠረችው ቤልጂየምን ካሸነፉ ብቻ ነበር።

ማክሰኞ ምሽት በተደረገው የሁለቱ ኃያላን እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ የፈረንሳይ የተከላካይ መስመር ተጫዋች ሳሙኤል ኡምቲቲ ባስቆጠራት ግብ አሁንም አሸንፈው መውጣት ችለዋል።

ፈረንሳይ በዚህኛው የዓለም ዋንጫ ለፍጻሜ የደረሰችው ከሃያ ዓመታት ጥበቃ በኋላ ነበር።

ክሮሺያ

እስካሁን ያደረገችውን 6 ጨዋታ በድል ያጠናቀቀችው ክሮሺያ በ21ኛው የሩሲያ የዓለም ዋንጫ ባደረገችው የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ ናይጄሪያን ሁለት ለባዶ በማሸነፍ ነው የጀመረችው። ክሮሺያ ባልተጠበቀ መልኩ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታዋ ላይ አርጀንቲናን 3 ለባዶ በማሸነፍ ከወዲሁ ከምድቧ ማለፏን ማረግገጥ ችላ ነበር።

የክሮሺያ የመጨረሻው የምድብ ጨዋታ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫው ከተሳተፈችው አይስላንድ ጋር ነበር። ጨዋታው አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቀቀ ተብሎ ሲጠበቅ፤ የፊት መስመር ተጫዋቹ ማሪዮ ማንዙኪች ዘጠናኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ግብ ሁለት ለአንድ ማሸነፍ ችለዋል።

ክሮሺያ ከምድባቸው ያለፉትን 16 ሃገራት ስኬታማ በሆነ መልኩ ተቀላቀለች። በመቀጠል ከሌላኛዋ የአውሮፓ ሃገር ዴንማርከ ጋር ነበር የተገናኘችው። እልህ አስጨራሽ የነበረው ይህ ጨዋታ በመደበኛው ሰዓት አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት ነበር ያለቀው። በተጨማሪው ሰዓትም ምንም ግብ ያልተቆጠረ ሲሆን፤ ጨዋታው ወደ ፍጹም ቅጣት ምት አምርቷል።

ግብ ጠባቂያቸው ዳንኤል ሱባሲች ሦስት ኳሶችን በማዳን ኮከብ ሆኖ ባመሸበት ጨዋታ ክሮሺያ ሦስት ለሁለት በማሸነፍ ወደ ፍጻሜው የሚያደርጉትን ጉዞ አሳምረዋል።

Image copyright AFP/GETTY IMAGES

በሩብ ፍጻሜው ደግሞ ባልተጠበቀ መልኩ ስፔንን በማሸነፍ ወደ መጨረሻ ስምንት ውስጥ ከገባችው አዘጋጇ ከሩሲያ ጋር ተገናኘች። ይህም ጨዋታ በመደበኛው ሰዓት ሁለት ለሁለት በሆነ አቻ ውጤት የተጠናቀቀ ሲሆን፤ በተጨማሪውም ሰዓት ምንም ግብ ሳይቆጠር ተጠናቀቀ።

ክሮሺያም ከምድቧ ካለፈች በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ በፍጹም ቅጣት ምት ሩሲያን አራት ለሦስት በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቀለች።

ረቡዕ ምሽት በተደረገው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ክሮሺያ ከእንግሊዝ ነበር የተገናኘችው። ገና ጨዋታው እንደተጀመረ በተቆጠረባቸው ግብ ያልተደናገጡት ክሮሺያዎች የጨዋታው ኮከብ በነበረው አይቨን ፔሪሲች አማካይነት 68ኛው ደቂቃ ላይ አቻ መሆን ቻሉ።

ጨዋታው በዚሁ አቻ ውጤት ተጠናቆ ለሦስተኛ ጊዜ ክሮሺያ ወደ ተጨማሪ ሰዓት አመራች። በዚህ ጨዋታ ግን ተጨማሪው ሰዓት ከማለቁ በፊት ባስቆጠሯት ሁለተኛ ግብ በዓለም ዋንጫ ታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ለፍጻሜው ጨዋታ መድረሳቸውን አረጋገጡ።