ጅማ አባጅፋር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ሆነ

የጅማ አባጅፋር አርማ Image copyright የጅማ አባጅፋር ፌስቡክ ገጽ

እስከ መጨረሻዎቹ ሁለት ሳምንታት ድረስ ሶስት ክለቦችን ያፎካከረውና አሸናፊውን ለመለየት እስከ ዛሬው ጨዋታ ድረስ በጉጉት ያስጠበቀው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ፍጻሜውን አግኝቷል።

ፕሪምየር ሊጉን ዘንድሮ የተቀላቀሉት ጅማ አባጅፋሮች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ሆነዋል።

ጅማ አባጅፋር ከአዳማ ከተማ ጋር በሜዳቸው ጅማ ላይ ዛሬ በ8 ሰዓት ደረጉትን ጨዋታ 5 ለባዶ በማሸነፍ ነው ሻምፒዮን መሆናቸውን ያረጋገጡት።

ከ30 ጨዋታ 55 ነጥብ መሰብሰብ የቻሉት ጅማ አባጅፋሮች ቀላል የሚባል አመት አላሳለፉም። ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ጣራ ለምመጣት ከፍተኛ ትግል አድርገው ነበር።

''ብሔርተኝነት'' እያጠላበት ያለው እግር ኳስ

ዛሬ በተመሳሳይ 8 ሰዓት በተደረገው የሰላሳኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ሌላኛው ለዋንጫው የተጠበቁትን ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከሃዋሳ ከተማ አገናኝቷል።

በጨዋታው 2 ለባዶ ያሸነፉት ጊዮርጊሶች የጅማ አባጅፋርን ውጤት እስኪሰሙ ድረስ በአዲስ አበባ ስታዲየም የተቀመጠውን ዋንጫ እንደሚያነሱት ተስፋ አድርገው ነበር።

ከጨዋታው በፊት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከ29 ጨዋታዎች 52 ነጥብ በመሰብሰብ ከጅማ አባጅፋር ጋር ተመሳሳይ ነጥብና የግብ ልዩነት ይዘው፤ ብዙ ባገባ በሚለው ህግ በፕሪምየር ሊጉ ሰንጠረዥ አናት ላይ ተቀምጠው ነበር።

ከጨዋታዎቹ መጠናቀቅ በኋላ ግን ጅማ አባጅፋር በ55 ነጥብና 24 የግብ ልዩነት አንደኛ ሆኖ ሲጨርስ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ሆኖ ጨርሷል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ቡና ባለፈው አርብ መቐለ ከተማን 3 ለ 1 በማሸነፍ በ50 ነጥብ ሶስተኛ ሆኖ የጨረሰ ሲሆን፤ አርባምንጭ ከተማ፤ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እንዲሁም ወልዲያ ከነማ ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መውረዳቸውን አረጋግጠዋል።

ቅዳሜ ዕለት የመውረድ አደጋ ተጋርጦበት የነበረው ድሬዳዋ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ሰንጠረዥ 13ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ያረጉት ጨዋታ በዝናብ ምክንያት ቢቋረጥም፤ ጨዋታው እሁድ በድጋሚ ተካሂዶ ድሬዳዋ ከተማ 2 ለባዶ በማሸነፍ 35 ነጥብ በመያዝ በፕሪምየር ሊጉ መቆየቱን አረጋግጧል።

የጅማ አባጅፋሩ አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ ዛሬ ያስቆጠራቸውን 4 ግቦች ጨምሮ በ23 ግብ የአመቱ ኮከብ ጎል አግቢ ሆኖ ጨርሷል። የኢትዮጵያ ቡናው ሳሙኤል ሳኑሚ በ13 ግብ ሁለተኛ እንዲሁም የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አል ሃሰን ካሉሻ በ13 ግብ ሶስተኛ ሆነው ጨርሰዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ