ሞሃመድ ሳላህ በፊፋ ምርጥ የወንድ ተጫዋች የመጨረሻ ሶስት ውስጥ ገባ

ሞሃመድ ሳላህ፤ ክርስቲያኖ ሮናልዶ፤ ሉካ ሞድሪች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ፤ ሉካ ሞድሪች እና ሞሃመድ ሳላህ የፊፋ የ2018 ምርጥ የወንድ ተጫዋች ምርጫ የመጨረሻ ሶስት ውስጥ ገብተዋል። የባርሴሎና እና የአርጀንቲና አጥቂ እንዲሁም የአምስት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው ሊዮኔል ሜሲ የመጨረሻ ሶስት እጩዎች ውስጥ መግባት ሳይችል ቀርቷል።

የአለም ዋንጫን ካነሳው የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድንም ምንም አይነት ተጫዋች መግባት አልቻለም።

ከሊዮን ጋር የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ማንሳት የቻሉት የኖርዌዩዋ ኣዳ ሄገርበርግ እና ጀርመናዊቷ ዜኒፈር ማሮዝሳን እንዲሁም የብራዚሏ አጥቂ ማርታ በፊፋ የሴቶች ምርጥ ተጫዋች ዘርፍ የመጨረሻ ሶስት ውስጥ መግባት ችለዋል።

የፖርቹጋሉ የክንፍ መስመር ተጫዋች ሮናልዶ እ.አ.አ የ2016 እና 2017 የፊፋ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠ ሲሆን፤ ከሪያል ማድሪድ ጋር ደግሞ አምስት ጊዜ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ አሸንፏል።

ያልተዘመረለት ጀግና የሚባለው የሪያል ማድሪዱ ድንቅ አማካይ ሉካ ሞድሪች የ2018 የአለም ዋንጫ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል። በወቅቱም ከፈርንሳይ ጋር ለፍጻሜ ቢደርሱም፤ በፈረንሳይ አራት ለሁለት ሽንፈት ደርሶባቸዋል።

የግብጹ አጥቂ ሞሃመድ ሳላህ ደግሞ ቡድኑ ሊቨርፑል በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ለፍጻሜ ደርሶ በሪያል ማድሪድ በተሸነፈበት የውድድር ዓመት 44 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የአውሮፓ ምርጥ ወንድ ተጫዋች ምርጫ ሞድሪች፤ ሮናልዶ እና ሞሃመድ ሳላህን በመብለጥ አሸናፊ መሆን ችሎ ነበር።

የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድንን ለአለም ዋንጫ ድል ያበቃው የቀድሞ ተጫዋች የአሁኑ አሰልጣኝ ዲዲዬር ዴሾ፤ ክሮሺያን በአለም ዋንጫው ለፍጻሜ ያደረሰው አሰልጣኝ ዝላትኮ ዳሊች እና የቀድሞው የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ዚነዲን ዚዳን በምርጥ አሰልጣኝነት እጩ ውስጥ ተካተዋል።

እ.አ.አ በ2016 ፊፋ ከባሎንዶር ሽልማት ጋር ያለውን ግንኙነት ካቋረጠ በኋላ ሽልማቱ ለብቻው መካሄድ ጀምሯል።

በፊፋ የተወከሉ ታዋቂ ተጫዋቾችና ባለሙያዎች በእያንዳንዱ የሽልማት ዘርፍ በመጀመሪያው ዙር አስር ተጫዋቾችን በእጩነት ያቀርባሉ። በመቀጠል እያንዳንዳቸው 25 በመቶ ድምጽ ያላቸው ከብሄራዊ ቡድን አምበሎች፤ አሰልጠኞች፤ ስፖርት ጋዜጠኞች እና ደጋፊዎች የተውጣጣ የዳኞች ስብስብ አሸናፊውን ይመርጣል።

ከዚህ በተጨማሪ ሮናልዶ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ጨዋታ ጁቬንቱሳ ላይ በመቀስ ምት ያስቆጠራት ግብ እና የማድሪዱ አጥቂ ጋሬዝ ቤል በፍጻሜው ጨዋታ ሊቨርፑል ላይ ያስቆጠራት ተመሳሳይ የመቀስ ምት ግብ በምርጥ ጎል ዘርፍ ከታጩት አስር ግቦች መካከል መሆን ችለዋል።

አሸናፊዎቹ እ.አ.አ በመስከረም 24 ለንደን ውስጥ ይፋ የሚደረጉ ይሆናል።