የፖሊስን ጭካኔ በመቃወም በመንበርከክ የሚታወቀው ኮሊን ኬፐርኒክ የናይክ ኩባንያ መሪ አስተዋዋቂ ሆነ

የቀድሞው የሳንፍራንሲስኮ ፎርቲናይነር ኳርተር ባክ ቡድን ተጫዋች የሆነው ኮሊን ኬፐርኒክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ጥቁር አሜሪካዊው ኮሊን ኬፐርኒክ የአሜሪካ እግር ኳስ ተብሎ ከሚታወቀው ተጫዋችነቱ በላይ የፖሊስን ጭካኔ በመቃወም የብሔራዊ መዝሙር በሚዘመርበት ወቅት በመንበርከክ ይታወቃል።

ተግባባሩ አነጋጋሪነትን የፈጠረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ደግሞ ታዋቂው ኩባንያ ናይክ የማስታወቂያዎቹ ፊታውራሪ አድርጎታል።

የቀድሞው የሳንፍራንሲስኮ ፎርቲናይነር ኳርተር ባክ ቡድን ተጫዋች የሆነው ኮሊን ኬፐርኒክ "ጀስት ዱ ኢት" ( በተግባር እናውለው ) ለሚለው የናይክ መፈክር 30ኛ አመት ማስተዋወቂያ እንደሚሳተፍ ተገልጿል።

በአውሮፓውያኑ 2016 ኮሊን ኬፐርኒክ ፖሊስ በጥቁሮች ላይ የሚያደርሰውን ግድያና ጭካኔ እስካልተገታ ድረስ ለብሔራዊ መዝሙሩ አልነሳም በሚል ተቃውሞውን ጀመረ።

ተከትሎም ጥቁር ተጫዋቾች ተመሳሳይ ተቃውሞዎችን ማድረግ ጀመሩ።

እንደ ኮሊን ኬፐርኒክ የተንበረከኩ እንዳሉት ሁሉ ሌሎቹ ደግሞ እጃቸውን በማጣመር ለተቃውሞው ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋል።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተጫዋቾቹን በከፍተኛ ሁኔታ የአሜሪካን ሰንደቅ አላማ "ያዋረዱ" በማለት ከመተቸት በተጨማሪ "የውሻ ልጆች" የሚል ስድብና ከስራ ሊባረሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአሁኑ የናይክ ማስተዋወቂያ መፈክርም "ሁሉንም አይነት መስዋዕት የምንከፍልለት ቢሆንም፤ በአንድ ነገር እንመን" የሚል ነው።

በዚህ ማስታወቂያ ውስጥ ከተካተቱት መካከል ኮሊን ኬፐርኒክ፣ በአሜሪካ የብሔራዊ እግርኳስ ሊግ ታዋቂ ተጫዋች ኦዴል ቤካም ጁኒየርና ሻኪም ግሪፊንና ታዋቂዋ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች ሴረና ዊልያምስ ይገኙበታል።

በትናንትናውም ዕለት ተጫዋቹ በትዊተር ገፁ ላይ ማስታወቂያውንና መፈክሩን አስፍሯል።

በሰሜን አሜሪካ የናይክ ኩባንያ ምክትል ፕሬዚዳንት ጂኖ ፊሳኖቲ ለሀገሪቱ ሚዲያ እንደተናገሩት " ኮሊን ኬፐርኒክ ትውልዱን ማነሳሳት የቻለ አትሌት ነው። የስፖርትንም ኃይል በመጠቀም አለምን ወደፊት አንድ እርምጃ አሻግሯል" ብለዋል።

የ30 ዓመቱ ኮሊን ኬፐርኒክ በአውሮፓውያኑ 2011 ከናይክ ኩባንያ ጋር ስፖንሰር ጋር በተገናኘ ስምምነት ላይ የደረሰ ሲሆን በመንበርከክም ተቃውሞውን ሲገልፅም የናይክ ኩባንያ ክፍያ አልተቋረጠም ነበር።

ኮንትራቱ ከክለቡ ሳንፍራንሲስኮ ፎርቲናይነር ኳርተር ባክ በባለፈው አመት የተቋረጠ ሲሆን በተቃውሞየ የተነሳ ነው በሚልም ክስ ላይ ነው።

በዚህ አመትም የአሜሪካ የብሔራዊ እግርኳስ ሊግ ብሔራዊ መዝሙር በሚዘመርበት ወቅት ተጫዎቾች ከተንበረከኩ በአዲሱ ፖሊሲ መሰረት ቅጣት እንደሚጠብቃቸው መገለፁ የሚታወስ ነው ።

ሊጉ እንዳሳወቀው ሰንደቅ ዓላማው ከፍ በሚልበት ወቅት መቆም የማይፈልጉ እስኪያልቅ ድረስ መልበሻ ክፍል መቆየት ይችላሉ።

ሊጉ ለሰንደቅ ዓላማውና ለብሔራዊ መዝሙሩ ክብር የሌላቸው የቡድኑ አባላት ተመጣጣኝ ቅጣት እንደሚጠብቃቸውም አስታውቆ ነበር።