የሃገራት ሊግ ምንድነው?

የፈረንሳይ እና የጀርመን ጨዋታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሁሉንም እግር ኳስ አፍቃሪ ቀልብ ይዞ ከቆየው የዓለም ዋንጫ መጠናቀቅ በኋላ ቀንሶ የነበረው የእግር ኳስ ተመልካች ቁጥር የአውሮፓ ሊጎች ሲጀመሩ እንደገና አንሰራርቷል።

እስካሁን አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች የተደረጉበት እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ገና ከአሁኑ ፉክክሩ ተጧጡፏል። ሊቨርፑል፣ ቼልሲና ዋትፎድ ከአራት ጨዋታ 12 ነጥቦችን በመሰብሰብ ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ቦታ ይዘዋል።

በሁሉም ጨዋታ ሽንፈትን ያስተናገደው ዌስት ሃሞ ደግሞ የመጨረሻውን ሃያኛ ቦታ ይዟል።

በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ ከሦስት ጨዋታ ሦስቱንም በማሸነፍ የላሊጋው አሸናፊ ለመሆን የሚያደርጉትን ትንቅንቅ ከጅምሩ ተያይዘውታል።

በአዲሱ የፊፋ አሰራር መሰረት በዚህ ሳምንት ሁሉም የአውሮፓ ሊጎች የውስጥ ውድድር አያካሂዱም። ይህም የሚሆነው ትርጉም የለሽ ያላቸውን የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማስቀረት በማለት ፊፋ ያዘጋጀው የሃገራት ሊግ ሐሙስ ዕለት ስለጀመረ ነው።

በመክፈቻው ዕለትም የዘንድሮው የአለም ዋንጫ አሸናፊ ፈረንሳዮች ከ2014 አሸናፊዎቹ ጀርመኖች ጋር የተገናኙ ሲሆን፤ ጨዋታውም ምንም ግብ ሳይቆጠርበት አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በዚህኛው የዓለም ዋንጫ ከፈረንሳይ ጋር ለፍጻሜ ደርሳ 4 ለ 2 በሆነ ውጤት የተሸነፈችው ክሮሺያም ከፖርቹጋል ያደረገችውን ጨዋታ 1 ለ 1 በሆነ የአቻ ውጤት አጠናቃለች።

በአዲሱ አሰልጣኝ ሪያን ጊግስ የሚመሩት ዌልሶች በበኩላቸው ከአርላንድ ያደረጉትን ጨዋታ 4 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፈዋል። አሰልኙኙ ጊግስም በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያ ሦስት ነጥብን ማግኘት ችሏል።

ፊፋ ሃገራት የቅድመ ዝግጅት ጨዋታዎችን ትኩረት ሰጥተው በደንብ እንዲጫወቱ ይረዳል ብሎ ያዘጋጀው አዲሱ የሃገራት ሊግ ውድድር 55 ሃገራትን ያሳትፋል።

የሃገራቱ ምድቦችም የሚወሰኑት ፊፋ በሚያወጣው ዓመታዊ የዓለም ሃገራት ብሔራዊ ቡድን ደረጃ ሲሆን፤ ሦስት ወይንም አራት አባላት ይኖሩታል።

በዚህ መልኩ የሚካሄደው ውድድር እ.አ.አ በወርሃ ሰኔ 2019 ፍጻሜውን የሚያገኝ ሲሆን፤ አሸናፊው ብሄራዊ ቡድን የሃገራት ሊግ ሻምፒዮን የሚባል ይሆናል።

ቅዳሜና እሁድ ከሚደረጉ ሌሎች ጨዋታዎች መካከል እንግሊዝን ከስፔን የሚያገናኘው ጨዋታ ተጠባቂ ከሚባሉት መካከል ነው።