ማርሻል፣ ሳላህ፣ ማኔ፣ ባርክሌይ፣ ፔሬራ ቡድኑ ውስጥ ተካተዋል

ሉካስ ፋቢያንስኪ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በሳምንቱ መጨረሻ በተደረጉ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ሊቨርፑል ካርዲፍን በቀላሉ ሲያሸንፍ ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ ኤቨርተንን በማሸነፍ ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ አናት ለመጠጋት የሚያደርገውን ጉዞ አሳምሯል።

ዋትፎርድና ቦርንማውዝ ሦስት ነጥብ ሲያገኙ፤ ዌስትሃም ከሌስተር አቻ ተለያይተዋል።

ነገር ግን የትኞቹ ተጫዋቾች ድንቅ ብቃታቸውን አሳይተው የጋሬዝ ክሩክስ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ መግባት ቻሉ?

ግብ ጠባቂ- ሉካስ ፋቢያንስኪ (ዌስትሃም)

ዌስትሃም ከሌስተር አንድ አቻ በተለያየበት ጨዋታ ፋቢያንስኪ ድንቅ ነበር። ሌስተሮች ይህንን ግብ ጠባቂ አልፈው ጎል ማስቆጠር እጅግ ከብዷቸው ነበር። ፖላንዳዊው ኢንተርናሽናል በዚህ ጨዋታ ብቻ ሰባት ያለቀላቸው ኳሶችን ግብ ከመሆን አድኗል።

ተከላካዮች- ፓብሎ ዛባሌታ (ዌስትሃም)ቪክቶር ሊንድሎፍ (ዩናይትድ)ፋቢያን ባልቡዌና (ዌስትሃም)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፓብሎ ዛባሌታ: ይህ ተጫዋች በሰላሳዎቹ አጋማሽ የሚገኝ ቢሆንም፤ በሜዳ ላይ ያለው ጉልበትና ተነሳሽነት አስገራሚ ነው። የሌስተሩን የፊት መስመር ተጫዋች ዊልፍሬድ ንዲዲን ፋታ ነስቶት ነበር።

ዛባሌታ ቡድኑ ከሌስተር ሲቲ አቻ ሲለያይ ከቡድኑ አጋሮቹ በተሻለ 64 ኳሶችን ነክቷል።

ቪክቶር ሊንድሎፍ : ሊንድሎፍ ከዚህ በፊት ሲጫወት በሚሠራቸው ስህተቶች ምክንያት ይህ ተጫዋች ማንቸስተር ውስጥ ምን ይሠራል ብዬ ነበር። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ያሳው ብቃት ግን ሃሳቤን አስቀይሮኛል።

ማንቸስተር ኤቨርተንን 2 ለ 1 ሲያሸንፍ ተከላካዩ ሊንድሎፍ ብዙ ኳሶችን ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በተሳካ ሁኔታ ያርቅ ነበር።

ፋቢያን ባልቡዌና : እንደዚህ ተከላካይ ልፋት ቢሆን ኖሮ ቡድኑ ዌስትሃም ከሌስተሩ ጨዋታ ሶስት ነጥብ ይዞ መውጣት ነበረበት። ምንም እንኳን ለቡድኑ ብቸኛዋን ለራሱ ደግሞ በዌስትሃም የመጀመሪያውን ግብ ቢያስቆጥርም፤ ሌስተሮች የመቷት ኳስ እሱን ነክታ ነው ግብ የተቆጠረባቸው።

አማካዮች- ሮቤርቶ ፔሬራ (ዋትፎርድ)ሎፍተስ ቺክ (ቼልሲ)ሉካ ሚሊቮቪች (ክሪስታል ፓላስ)ሮዝ ባርክሌይ (ቼልሲ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሮቤርቶ ፔሬራ: ፔሬራ ሃደርስፊልድ ላይ ያስቆጠራትን አይነት ግብ ከዚህ በፊት ያየሁት በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር የ1981 ኤፍ ኤ ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ ላይ የቶተንሃሙ ሪኪ ቪላ የማንቸስተር ሲቲ ግማሽ ተጫዋቾችን ሸውዶ ግብ ሲያስቆጥር ነው።

በቅዳሜው ጨዋታ ያየሁት የዚህን ግብ ተመሳሳይ ነው። አርጀንቲናውያን እንደዚህ አይነት ተአምራዊ ግብ ማስቆጠር ልማዳቸው ነው። በአጭሩ ያስቆጠራት ግብ እጅግ አስገራሚ ነበረች።

እስካሁንም ሁለት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ሲያቀብል፤ ስምንት ግቦች ደግሞ በስሙ አስመዝግቧል።

ሎፍተስ ቺክ: እንግሊዛዊው አማካይ ባለፈው ሃሙስ በአወሮፓ ሊግ ቼልሲ ቤት ቦሪሶቭን ሲያሸንፍ ሃትሪክ የሰራ ሲሆን፤ በፕሪምየር ሊጉ ደግሞ በርንሌይን ሲያሸንፉ አንድ ጎል አስቆጥሯል።

ሰላሳኛው ደቂቃ ላይ በፔድሮ ተቀይሮ የገባው ሎፍተስ ቺክ አሰልጣኙን አላሳፈረም። በዚህ ብቃቱ ከቀጠለ የቼልሲ ተስፋ በእጁ ሊሆን ይችላል።

ሉካ ሚሊቮቪች: ባለፈው ሳምንት ክሪስታል ፓላስ ከኤቨርተን ሲጫወት ፍጹም ቅጣት ምት ስቶ ነበር። ከአርሰናል በነበራቸው ጨዋታ ግን ያገኙትን ፍጹም ቅጣት ምት ያለምንም ስህተት ወደ ግብነት ቀይሯታል።

በድጋሚ ያገኙትን ፍጹም ቅጣት ምትም በማስቆጠር ቡድኑ አንድ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ረድቷል።

ሮዝ ባርክሌይ: ባርክሌይ ኤቨርተንን ለቅቆ ወደ ቼልሲ ሲያመራ ስኬታማ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም ነበር። ከሰሞኑ እያሳየው ያለው መሻሻል ግን አስገራሚ ነው።

ሞራታ ለቼልሲ የመጀመሪያዋን ግብ ሲያስቆጥር ባርክሌይ ነበር አመቻችቶ ያቀበለው። በጨዋታው አንድ ግብም ሲያስቆጥር፤ ሁለት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል።

አጥቂዎች- ሳዲዮ ማኔ (ሊቨርፑል)ሞሃመድ ሳላህ (ሊቨርፑል)አንቶኒ ማርሻል (ዩናይትድ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሳዲዮ ማኔ: ቅዳሜ ዕለት ካርዲፍ ላይ ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች እጅግ አስገራሚ ነበሩ። የነበረው ሀይል፣ ጉልበትና አጠቃላይ ብቃት ለሊቨርፑል ትልቅ መነሳሳትና የግብ እድሎችን ፈጥሯል።

ከሞሃመድ ሳላህ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብለው ያስቆጠሯት አራተኛ ግብ የዚህ ማሳያ ናት። ማኔ ከሳውዝሃምፕተን ወደ ሊቨርፑል ሲመጣ የነበረውን ብቃት በድጋሚ እያሳየን ነው።

ሞሃመድ ሳላህ: ሊቨርፑሎች አንድ እጃቸው ከጀርባቸው ጋር ታስሮ እንዲሁም አይናቸው በጨርቅ ተሸፍኖ ቢሆን ኖር እንኳን የካርዲፉን ጨዋታ በቀላሉ ያሸንፉ ነበር።

ሳላህ በቻምፒየንስ ሊጉ ያስቆጠራቸውን ሁለት ግቦች በአግባቡ አጣጥሞ ሳይጨርስ ነው ወደዚህ ጨዋታ የመጣው። ቡድኑንም በሚገባ ሲያገለግል ነበር። ለሊቨርፑልም የመጀመሪያዋን ግብ ያስቆጠረው እሱ ነው።

ሞሃመድ ሳላህ ለሊቨርፑል በ35 ጨዋታዎች 33 ግቦች ማስቆጠሩን ያውቃሉ?

አንቶኒ ማርሻል: የሆዜ ሞሪንዮው ዩናይትድ ከኋላ ተነስቶ ሲጫወት ለተመልካች አስደሳች ነው። ግብ አግብተው ከሆነ ግን ጨዋታቸው ብዙም ደስ አይልም።

ደግነቱ ለዩናይትዶች አንቶኒ ማርሻልና ፖል ፖግባ ጥሩ እየተንቀሳቀሱ ነው። ዩናይትድ ባለፈው ሳምንት ከቼልሲ ሲጫወት ሁለቱንም ግቦች ያስቆጠረው ማርሻል ነበር። በዚህ ሳምንትም የማሸነፊያዋን ሁለተኛ ግብ በአስገራሚ ሁኔታ አስቆጥሯል።

እስካሁን በተሰለፈባቸው ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች አራት ግቦችን አስቆጥሯል።