"የዘረኝነት ጥቃቱ ከዚህም በላይ ሊከፋ ይችላል" ንጎሎ ካንቴ

የቶትንሃምና የቼልሲ ተጫዋቾች ሜዳ ውስጥ Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የቶትንሃምና የቼልሲ ተጫዋቾች ሜዳ ውስጥ

ትናንት ምሽት በነበረው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ቶትንሃም ከቼልሲ ጋር ሲጫወቱ በጥቁር ተጫዋቾች ላይ በተለይም በቼልሲው ተከላካይ አንቶንዮ ሩዲገር ላይ ያነጣጠረ የዘረኝነት ስድብ ከደጋፊዎች በኩል ተሰምቷል።

ይህንንም ተከትሎ የአገሪቱ ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ተጫዋቾች ማህበር መንግሥት ከእግር ኳስ ጨዋታዎች ላይ የሚከሰቱትን የዘረኝነት ድርጊቶች መርምሮ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።

የቶተንሃም ቡድንም በክስተቱ ላይ ጥልቅ ምርመራ እንደሚያደርግና "ጠንከር ያለ እርምጃ" እንደሚወስድም አሳውቋል።

በጥቁር ተጫዋቾች ላይ የተሰነዘረውን የዘረኝነት ድርጊት ተከትሎ ጨዋታው ለአጨር ጊዜ ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፤ በስታዲየሙ ውስጥ ባሉ የድምጽ ማጉያዎች በኩል "የዘረኝነት ባህሪ በጨዋታው ላይ እንቅፋት" እየሆነ መሆኑ ለተመልካቾች ተገልጾላቸዋል።

"እንዴት ለሴት ልጅ የወንዶች ክለብ ይሰጣል?' ተብሎ ነበር" መሠረት ማኒ

"በአንድ ጨዋታ ሰባት ግቦችን በማስቆጠር ታሪክ መስራቴ አስደስቶኛል" ሎዛ አበራ

«እግር ኳሰኞች ከማሕበራዊ ሚድያ እራሳቸውን ማግለል አለባቸው»

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረገው የቼልሲው የመሃል ሜዳ ተጫዋች ንጎሎ ካንቴ "የእግር ኳሱ የበላይ ኃላፊዎች ጉዳዩን በአንክሮ ካልመረመሩት የዘረኝነት ጥቃቱ ከዚህም በላይ የከፋ ሊሆን ይችላል" በማለት የጉዳዩን አሳሳቢነት ተናግሯል።

በጉዳዩ ላይ ከዚህም በላይ መነጋገር ለተጫዋቾች የግድ አስፈላጊ ነው ብሎ ያምናል ካንቴ።

በሁለተኛው አጋማሽ ደጋፊዎች ሲናገሩት የነበረው ነገር "አጸያፊ ነው፤ በእግር ኳስ ውስጥ ይህ መኖር አልነበረበትም። ነገር ግን ጤናማ እግር ኳስ ይኖረን ዘንድ እኛም ተገቢውን ምላሽ ሰጥተን ማስተካከል የሚኖርብን ይመስለኛል" ብሏል የቼልሲው ኮከብ።

በእርግጥ "የተባለውን ነገር አልሰማሁም ነበር" የሚለው ካንቴ የቡድኑ አምበል አዝፒሊኬታ ጉዳዩን ለዳኛው ሲያመለክት ነበር "ጥቃት እየሰነዘሩብን እንደነበር የገባኝና እኔም ማዳመጥ የጀመርኩት" በማለት በጨዋታው የደረሰባቸውን የዘረኝነት ጥቃት እንዴት እንደተረዳ ለቢቢሲ አስረድቷል።

ይህንን ድርጊት ለማስተካከል በየደረጃው የሚገኙ የእግር ኳሱ የበላይ ጠባቂዎች የመፍትሔ አማራጮችን እንዲያስቀምጡም ካንቴ ጥሪውን አቅርቧል።

"ዳኞች አሉ፣ የፕሪሚየር ሊጉ የበላይ አካል አለ፤ ስለዚህ እነሱ መፍትሔ ያመጣሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። መፍትሔው እንዲመጣ ግን የሆነውን ነገር ለሚመለከታቸው አካላት ማመልከት ከእኛ የሚጠበቅ ነው" ያለው ካንቴ "ችግሩን ለመቅረፍ እየሞከሩ እንደሆነ አምናለሁ፤ ነገር ግን እንዴት ሊያስተካክሉት እንደሚችሉ በጋራ የምናየው ይሆናል ብሏል የፈረንሳይና የቼልሲው የመሃል ሜዳ ተጫዋች ንጎሎ ካንቴ።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ