ማንችስተር ሲቲ ላይ የተጣለው ቅጣት በአሰልጣኙና በተጫዋቾቹ ላይ ምን ውጤት ይኖረዋል?

የማንችስተር ሲቲ አርማ Image copyright PA Media

ማንችስተር ሲቲ የአውሮፓ እግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪ የሆነውን አካል የፈቃድና የገንዘብ አጠቃቀም ደንብን በመጣሱ ለቀጣይ ሁለት የውድድር ዘመኖች በሚደረጉ የአውሮፓ ክለቦች ውድድር ላይ እንዳይሳተፍ እገዳ ተጣለበት።

ከዕገዳው በተጨማሪ ቡድኑ የሰላሳ ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ቅጣት የተጣለበት ሲሆን በፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች ካገኘው ነጥብ ላይ ሊቀነስበት እንደሚችልም ተጠቅሷል።

ይህ የዕገዳና የቅጣት ውሳኔ የስፖርት ጉዳዮች ግልግል ፍርድ ቤት ላይ ይግባኝ ሊባልበት የሚችል እንደሆነም ተነግሯል። ቡድኑም በቅጣት ውሳኔው መሳዘኑንና ሕግን ያልተከተለ መሆኑን ገልጾ ይግባኝ እንደሚጠይቅ ገልጿል።

የቡድኖችን የገንዘብ ሁኔታ የሚቆጣጠረው አካል እንዳለው ማንችስተር ሲቲ ለአራት ዓመታት ከስፖንሰር ያገኘውን ገቢ ደንብ ተላልፎ፣ አንሮ በማሳወቅና ሌሎች ጥሰቶች፣ በተጨማሪ በምርመራው ሂደት ለመተባበር ፈቃደኛ አልነበረም ብሏል።

የቅጣቱ ውሳኔ በይግባኝ እስካልተቀለበሰ ድረስ ቡድኑ ከሁለት የታላቁ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ውድድር ውጪ የሚሆን ሲሆን ይህም ለቡድኑም ሆነ ለአሰልጣኙ ትልቅ ጉዳትን ያስከትላል።

በአውሮፓ የሻምፒዮን ሊግ ውድድር ላይ መታየት ለተጫዋቾችና ለአሰልጣኞች እንደአንድ ስኬት ስለሚቆጠር ቅጣቱ ቡድኑ ውስጥ ያሉትን አሰልጣኞችና ተጫዋቾችን ሊያሸሽ እንዲሁም ሌሎችን ለመቅጠር እንቅፋት ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አለ።

እኤአ እስከ 2021 በማንችስተር ሲቲ ውስጥ ለመቆየት ኮንትራት የፈረመው ፔፕ ጋርዲዮላና ሌሎች እሱን ተከትለው ክለቡን የተቀላቀሉት ተጫዋቾች፣ ቡድኑ በታላቁ የአውሮፓ ክለቦች የውድድር መድረክ ላይ ለሁለት ተከታታይ ወቅቶች የማይሳተፍ ከሆነ ሲቲ ውስጥ የመቆየታቸው ነገር አጠያያቂ ነው።

ይህ ደግሞ በዓመታት ውስጥ አሉ ከተባሉ የእንግሊዝ እግር ኳስ ቡድኖች መካከል ለመሰለፍ ከፍተኛ ገንዘብን በማፍሰስ ስሙን የገነባውን ቡድን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሊጥለው ይችላል።

የሲቲ ባለስልጣናት ግን የተባለው አይነት ቅጣት እንዲጣልባቸው የሚያደርግ አንዳችም ጥፋት አለመስራታቸውን ለአሰልጣኙ ጋርዲዮላ ያረጋገጡላቸው ሲሆን፣ ይህ ተጫወቾችንም እንዲረጋጉና ቡድኑ ውስጥ እንዲቆዩ ያግዛል።

ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን የስፖርት ጉዳዮች የግልግል ፍርድ ቤት በማንችስተር ሲቲ ላይ የተጣለውን ቅጣት ተገቢ አይደለም ብሎ ካነሳው ነው።

ቡድኑም ጉዳዩን በቀላሉ እንደማይተወው አሳውቋል።